Fana: At a Speed of Life!

የጀርመን መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ አዲስ አበባ ገቡ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 26 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሁለት የአፍሪካ ሀገራት ይፋዊ የስራ ጉብኝት የሚያደርጉት የጀርመን መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ አዲስ አበባ ገብተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ብርቱካን አያኖ መራሄ መንግስቱ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

የጀርመን መንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ ባለሃብቶችና የተቋማት መሪዎች ዛሬ ኢትዮጵያ የመጣው ልዑክ ቡድን አባላት መሆናቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ አለም በዛሬው መግለጫቸው አስታውቀዋል።

በመራሄ መንግስቱ የሚመራው ልዑክ ከዛሬ ሐሙስ እስከ ቅዳሜ ድረስ በኢትዮጵያ እና በኬንያ ጉብኝት እንደሚያደርግ ይጠበቃል።

ሾልዝ በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ ከመንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ጋር ተገናኝተው የሚመክሩ ሲሆን የአፍሪካ ህብረትንም ይጎበኛሉ ተብሏል።

በአየር ንብረት ለውጥ ፣ በኢኮኖሚ ትብብር ፣ ቀጠናዊ ሰላምና የወቅቱን የሱዳን ግጭት መቆጣጠር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ይወያያሉም ነው የተባለው።

ሾልዝ የመንግስት መሪ ሆነው በአፍሪካ ለሁለተኛ ጊዜ የሚያደርጉትን ጉብኝት ነው ዛሬ በአዲስ አበባ የጀመሩት።

ስልጣን ከያዙ 6 ወራት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በኒጀር፣ ሴኔጋልና ደቡብ አፍሪካ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።

በበርናባስ ተስፋዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.