Fana: At a Speed of Life!

የመተንፈሻ አካላት መድከም ምንድን ነው?

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የመተንፈሻ አካላት ሥራቸውን በአግባቡ ማከናወን ሲያቅታቸው የመተንፈሻ አካል መድከም እንደሆነ ይገለጻል፡፡

የመተንፈሻ አካል ከአፍንጫ ጀምሮ በጉሮሮ የሚያልፍ ቱቦን እና ሳንባን የሚያካትቱ የአካል ክፍሎች ናቸው፡፡

ኦክስጂንን ጨምሮ ናይትሮጂን እና ጠቃሚ ዓየር ወደ ሰውነት ውስጥ ማስገባት እንዲሁም የተቃጠለና የማያስፈልግ ዓየርን ማስወጣትም ከሥራዎቻቸው መካከል መሆናቸው ይታወቃል፡፡

ሥራቸውን በአግባቡ ማከናወን ከአቃታቸው የመተንፈሻ አካል የጤና ዕክል ገጥሟቸዋል ማለት ነው ይላሉ ባለሙያዎች፡፡

በደም ውስጥ ያለው የኦክስጂን መጠን ከ60 ሚሊ ሜትር ኦፍ ሜርኩሪ በታች ከሆነ አንድ ሰው በቂ ኦክስጂን ማግኘት እንዳልቻለ ይገለጻል፡፡

የመተንፈሻ አካላት የተቃጠለ ዓየርን ማስወጣት ሲያቅታቸው ካርበንዳይ ኦክሳይድ በሰውነት ውስጥ ይበዛል ይላሉ፡፡

የተቃጠለ ዓየር ከ45 ሚሊ ሜትር ኦፍ ሜርኩሪ በላይ ከሆነ አንድ ሰው ለመተንፈስ ደክሟል እንደሚባል እና አንዳንድ ጊዜም የመተንፈስ ሥራ መሥራት እንደሚያቅተው ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የድንገተኛና ጽኑ ህሙማን ትምህርት ክፍል ኃላፊ ዶ/ር መንበኡ ሱልጣን እንዳሉት÷ የመተንፈሻ አካላት ህመም እስከ ሞት ያደርሳል፡፡

የከንፈር መጥቆር፣ የፍርሃት ስሜት መኖር፣ ላብ ላብ ማለት፣ ራስን መሳትና ማንቀጥቀጥ የኦክስጂን ዕጥረት ባጋጠመው ሰው ላይ ከሚታዩ ምልክቶች መካከል ይጠቀሳሉ ይላሉ፡፡

እንዲሁም ከባድ ራስ ምታት፣ የድካም ስሜትና ማንቀጥቀጥ ካርበንዳይኦክሳይድ ማስወጣት ያቃተው ሰው ምልክቶች መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

ሳንባን ከሚያጠቁ  ህመሞች እራስን በመጠበቅ  የመተንፈሻ አካላትን ተጋላጭነት መቀነስ እንደሚቻልም ያነሳሉ፡፡

በተጨማሪም ኢንፍሎዌንዛ እና የኮቪድ -19ን ጨምሮ በቀላሉ በቫይረስ የሚመጡ የመተንፈሻ አካላት ህመምን በክትባት መከላከል እንደሚቻልም ነው ያመላከቱት፡፡

አንዳንዶቹ ህመሞች በተለይ ካርበንዳይ ኦክሳይድን በአግባቡ ለማስወጣት የማያስችሉትን በመከላከል ብቻ ላይመለሱ እንደሚችሉም ነው የሚያስገነዝቡት፡፡

በመሆኑም መድኃኒቶችን ባለማቋረጥ ለመተንፈስ መቸገር እንዳያጋጥም ማድረግ ይቻላል ነው ያሉት፡፡

ዶ/ር መንበኡ ሱልጣን ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ የኒሞኒያ ኢንፌክሽን ያለባቸው፣ ሳል፣ የደረት ህመም፣ ትኩሳት፣ ብርድ ብርድ የሚል ስሜት ሲሰማቸው የመተንፈሻ አካል ህመም ሊሆን ስለሚችል ወደ ሕክምና ተቋም መሄድ እንደሚገባቸው ይመክራሉ፡፡

በየሻምበል ምህረት

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.