Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል በመኸር ወቅት 160 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማምረት ታቅዷል

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በ2015/16 ዓ.ም የመኸር ወቅት 160 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማምረት መታቀዱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል።

የቢሮው ኃላፊ ኃይለማርያም ከፍያለው (ዶ/ር) ዛሬ በሰጡት መግለጫ÷ በምርት ዘመኑ አምስት ሚሊየን ሔክታር በማረስ 160 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱን ተናግረዋል፡፡

ክልሉ በሰብል ምርት የሀገሪቱን 40 በመቶ ሽፋን እንደሚይዝ ጠቁመው÷ በቀጣዩ ዓመትም የተሻለ ምርት ለማምረት በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።

በምርት ዘመኑ የሚለማው መሬት ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ150 ሺህ ሔክታር ብልጫ አለው ነው ያሉት፡፡

ከሚለማው ውስጥም 2 ነጥብ 7 ሚሊየን ሔክታሩ በምግብ ሰብሎች የሚሸፈን መሆኑን ጠቅሰው÷ ከዚህም 95 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል ምርት ይጠበቃል ብለዋል፡፡

በዓመቱ በታቀደው መሰረት 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ሔክታሩ በኢንዱስትሪ ሰብሎች የሚሸፈን ሲሆን÷ ከዚህ ውስጥ 1 ነጥብ 1 ሚሊየኑን በስንዴ ሰብል ለመሸፈን መታቀዱን ገልጸዋል፡፡

በምርት ዘመኑ 10 ዓይነት ዋና ዋና ሰብሎች በክልሉ እንደሚለሙ እና ይህንም በአብዛኛው በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ ለማከናወን ታስቧል ነው ያሉት፡፡

ዕቅዱን ውጤታማ ለማድረግም 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ክልሉ ገብቶ 1 ነጥብ 4 ሚሊየኑን ለዩኒየኖች ማሰራጨት እንደተቻለ አንስተዋል፡፡

የአፈር ማዳበሪያ እጥትን ለመሸፈን በክልሉ 77 ሚሊየን ኩንታል የተፈጥሮ ማዳበሪያ መዘጋጀቱን ነው ሃላፊው የገለጹት፡፡
ዕቅዱ የተሳካ እንዲሆንም ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂዎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ ይደረጋል ብለዋል፡፡

በሙሉጌታ ደሴ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.