የጀርመን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ማድረግ በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ተደረገ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)የጀርመን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው መዋዕለንዋያቸውን ማፍሰስ በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ተደርጓል፡፡
በጀርመን ኢኮኖሚና የአየር ንብረት ጥበቃ ምክትል ሚኒስትር ዩዶ ፊሊፕ የተመራ የልዑካን ቡድን የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ የስራ እንቅስቃሴን ጎበኝቷል።
ለልዑካን ቡድኑ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ እና የኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ለሊሴ ነሚ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
ለልዑኩ በኢትዮጵያ መዋዕለንዋያቸውን ለሚያፈሱ ባለሃብቶች የሚቀርቡ ማበረታቻዎችንና የስራ ዘርፎችን እንዲሁም በኢንዱስትሪ ፓርኮች ያለውን የስራ እንቅስቃሴ አስመልክቶም ገለፃ መደረጉን ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የልዑካን ቡድኑ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ያለው የስራ እንቅስቃሴ አበረታች መሆኑን ገልፀው የጀርመን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለንዋያቸውን እንዲያፈሱ የድጋፍና ክትትል ስራዎችን እንደሚሰሩ ገልፀዋል።