የኢትዮጵያ የንግድ ልኡክ የፊታችን ግንቦት ወደ ፓኪስታን ያቀናል
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከፍተኛ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት እና የንግድ የልዑካን ቡድን በፈረንጆቹ ግንቦት 9 ወደ ፓኪስታን እንደሚያቀና በፓኪስታን የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ጀማል በከር ገልፀዋል።
ጉዞው በተለያዩ መስኮች የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን ትብብር ለማድረግ እና የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ያለመ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
አምባሳደር ጀማል በከር ÷ልኡካን ቡድኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ ኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችን ያካተተ 60 አባላትን ያቀፈ ነው ብለዋል።
የልዑካን ቡድኑ ከፓኪስታን አቻቸው ጋር በቴክኖሎጂ፣ ቱሪዝም እና ሌሎች ዘርፎች የመግባቢያ ስምምነት እንደሚፈራረሙም አምባሳደሩ ገልፀዋል።
እስከ ዛሬ ድረስ አነስተኛ የነበረውን የንግድ ልውውጥ ለማሳደግም በሁለቱም ሀገራት የንግድ ማህበረሰቦች መካከል የንግድ ስምምነቶች እንደሚፈረሙም ተናግረዋል።
አምባሳደር ጀማል በከር የሁለቱን ሀገራት የንግድ ግንኙነት በማሳደግና የሁለትዮሽ ንግድን ለማጠናከር በካራቺ እና ኢስላማባድ ከተሞች ሁለት የቢዝነስ ፎረሞች እየተዘጋጁ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የፓኪስታን የንግድ ማህበረሰብ በአዲስ አበባ ባደረጉት ጉብኝት በኢትዮጵያ የተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች እየታዩ ባሉ ለውጦች መደነቃቸውን ተከትሎ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የሁለትዮሽ የንግድ ልውውጥ ለማሳደግ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው አምባሳደሩ ገልፀዋል።
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ የንግዱ ማህበረሰብም ከአገሪቱ አቻዎቻቸው ጋር የንግድ ትስስር ለመፍጠር ፍላጎት እንዳላቸው መገለፁን ከኤምባሲው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።