የኢትዮጵያ የዲጂታል ፖሊሲዎች ሴቶችን ያካተቱ ተደርገው መዘጋጀታቸውን ጥናት አመላከተ
አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 28 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፉ የቴሌኮም ህብረት የቴሌኮሙኒኬሽን ልማት ቢሮ ኢትዮጵያ በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ያሏት ደንቦችና ፖሊሲዎች ውስጥ የሴቶችን ተካትቶ በሚመለከት ያስጠናውን የዳሰሳ ጥናት ይፋ አድርጓል።
በጥናቱ መሰረት ኢትዮጵያ በቅርቡ ባወጣቻቸው የዲጂታል ፖሊሲዎቿ ውስጥ ለሴቶች የተለየ ትኩረት ሰጥታለች ተብሏል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ጥናቱ የኢትዮጵያን የዲጂታል ክፍፍል በማሳየት በዲጂታል ስነ-ምህዳር ውስጥ ለስርዓተ-ፆታ ማካተት ምላሽ የሚሰጡ አዳዲስ ፖሊሲዎችን ለማዘጋጀት ያግዛል ብለዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በዲጂታል ስነ-ምህዳር ውስጥ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
የዓለም አቀፉ የቴሌኮም ህብረት የቴሌኮሙኒኬሽን ልማት ቢሮ ዋና ዳይሬክተር ኮስሞስ ዛቫ ዛቫ (ፒ ኤች ዲ) ጥናቱ የሴቶችን የዲጂታል ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያግዙ ምክረ ሃሳቦችን ያስቀመጠ እና በቀጣይ መደረግ ስላለባቸው ጉዳዮች አቅጣጫዎችን የሚጠቁም ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በፆታ፣ በእድሜ፣ በአካባቢ፣ በዲጂታል ክህሎት እና በሎሎችም የሚታይ የዲጂታል ክፍፍልን ለመቅረፍ ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር እየሰራ ነው ተብሏል።