መደመር የተበታተነን ጉልበት ወደ ጠንካራ ሀይል የሚቀይር ነው – ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም
አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 28 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) 5ኛውን ቀን የያዘው “ቃል ፤ተግባር፤ ትውልድ” በሚል በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የተዘጋጀው አውደ ርዕይ ዛሬም በአብርሆት ቤተ መጽሐፍት በመደመር መጽሐፍት ላይ ትኩረቱን አድርጎ ቀጥሎ ተካሂዷል ።
በአውደ ርዕዩ መደመር ፣ የመደመር መንገድ እና የመደመር ትውልድ መጽሐፍትን በካሊፎርኒያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህርና የህግ ባለሙያው አለማየሁ ገብረማርያም (ፕ/ር) ዳሰው ምልከታቸውን አቅርበዋል።
በዚህም የመደመር እሳቤን ከፍልስፍና፣ ከአተገባበር እና ከትውልድ አንጻር ተመልክተውታል።
መደመር ለኢትዮጵያ ችግር መፍትሔው በኢትዮጵያዊ እውቀት ፣ እምነት ፣ ታሪክ እና የተፈጥሮ ሀብት ውስጥ መሆኑን የሚያስረዳ እና የሚተገበር እሳቤ ነው ብለዋል።
መደመር የተበታተነን ጉልበት ወደ ጠንካራ ሀይል የሚቀይር እና ከመነጋገር ለውጥ እንደሚመጣ የሚያረጋግጥ መንገድ እንደሆነ መናገራቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል።