የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄና ውጤቶች የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄና ውጤቶች የፓናል ውይይት መድረክ በሚሊኒየም አዳራሽ እየተካሄደ ነው።
በውይይቱ ላይ የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል፣ የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር )፣ የጉምሩክ ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።
ከተጀመረ አንድ ዓመቱን ያስቆጠረው ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በማምረቻው ዘርፍ በርካታ ውጤቶችን አስገኝቷል ተብሏል፡፡
አቶ መላኩ አለበል በዚሁ ወቅት÷ የማምረቻው ዘርፍ ቀጣይነት ያለው እና ውድድር የበዛበት ዘርፍ ነው ብለዋል፡፡
በተለይም የኮሮና ቫይረስ መምጣት እና የጸጥታ ሁኔታውም ዘርፉን ይበልጥ ፈተና ላይ እንዲወድቅ እንዳደረገውም አንስተዋል ።
በዚህም የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም እንዲወርድ እና ኢንቨስትመንት እንዲቀዛቀዝ ማድረጉንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የተጀመረውም ቀደም ሲል ስንከተለው ከነበረው ነባራዊ ሁኔታ በመውጣት ና ችግሩን ለመቋቋም ያለመ ነው ብለዋል ።
በተጨማሪም በዘርፉ የነበሩ ማነቆዎችን በመለየት የተለየ መንገድ እንድንከተል የሚያስገድድ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በዚህ ዘርፍ በ10 ዓመቱ ዕቅድ ውስጥ ለ5 ሚሊየን ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር መታቀዱም ተጠቁሟል፡፡
በመሳፍንት እያዩ