በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አዘጋጅነት የሚካሄደው የመጻህፍት አውደርዕይ ተጠናቋል
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) 6ኛ ቀኑን የያዘው “ቃል፤ ተግባር፤ ትውልድ” በሚል መሪ ሀሳብ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አዘጋጅነት የሚካሄደው የመጻህፍት አውደርዕይ ተጠናቋል፡፡
በዛሬው የመጻሕፍት አውደርእይ ላይ የመደመር ትውልድ መጽሐፍን ታዳጊዎች የተረዱበትን እይታ ለታዳሚያን ያቀረቡ ሲሆን÷ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአውደርዕዩ ተኝተው መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልእክታቸውም በኢትዮጵያ እጣፈንታ ላይ ውሳኔን የምታሳልፉት የአሁኑ ትውልድ እናንተ ናችሁ ብለዋል።
“በእያንዳንዱ ግለሰብ ያለውን የእውቀት ጉድለት የሚሞላው ወንድሙ ነው፤ ያንን ለመሙላት ሁሉም ትውልድ ኃላፊነት አለበት” ብለዋል።
ሰው የሚሰማውንና የሚያየውን መምረጥ እንዳለበት ጠቅሰው÷በተለይ የአሁኑ ትውልድ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያ የሚያየውን መምረጥ አለበት ነው ያሉት፡፡
ሀገርን መገንባት አንድ ህፃን እንደማሳደግ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ህፃኑን ለማሳደግ በርካታ ኃላፊነትን መወጣት ያስፈልጋል፤ ኢትዮጵያም እንደዚያ ናት ብለዋል።
ትውልዱ ኢትዮጵያን የመገንባትና የማሳደግ ኃላፊነትም እንዳለበት ገልጸው÷የኢትዮጵያ ችግር የሚፈታው በትብብርና በመተጋገዝ ነው ብለዋል።
ታዳጊዎች በበኩላቸው÷የመደመር ትውልድ መጽሐፍ መተባበርና አብሮነትን በልዩነት እንደሚያነሳ አብራርተዋል፡፡
መጽሐፉ ኢትዮጵያዊነትን ከአፍሪካዊነት እንዲሁም አፍሪካዊነትን ከአለምአቀፋዊነት ጋር አዋህዶ እንደሚያብራራም ተረድተናል ብለዋል።
ኢትዮጵያን ለመገንባት የመደመር ትውልድ ትልቅ ኃላፊነት አለበት ያሉት ታዳጊዎች÷ ትውልዱ በእውቀት ዳብሮ ተሻጋሪ መሆን እንዲችል እንደ አብርሆትና ሳይንስ ሙዚየም የመሰሉ የትውልድ መቅረጫ ተቋማት ማሳያ ናቸው ብለዋል።
በተለይ የነገውን ትውልድ ለመገንባትና የዲሞክራሲ አረዳድ እንዲስፋፋ መሠረተ ልማቶች በየክልሎቹና በየገጠሩ መገንባት ይኖርባቸዋል ሲሉም ተናግረዋል።
በመጽሐፉ ውስጥ ስለመልካም ዘር የተወሳበትን ምዕራፍ ያቀረበችው ታዳጊ እየሩሳሌም ሰለሞን÷ የአሁኑ ትውልድ ለወደፊቷ ኢትዮጵያ ተስፋ ነው ብላለች።
የአሁኑ ትውልድ ተስፋነቱን በተግባር ማረጋገጥ እንዳለበት ጠቅሳ÷በሁሉም ረገድ ኃላፊነት እንዳለበት፣ በተለይ ደግሞ በንግግርና ውይይትም ማመን እንዳለበት ተናግራለች።
ታዳጊ ቅድስት በበኩሏ÷ለነገው ትውልድ የምትሻገረው ኢትዮጵያ ሰላሟ የፀናና ታሪኳን ያልዘነጋች እንድትሆን መስራት አለብን ብላለች።
በተለይ ደግሞ ያለፈውን የኢትዮጵያ ታሪክ ዘንግተን በሽኩቻና በግጭት ያልሆነ አዙሪት ውስጥ ከመግባት ወጥተን የነገዋን ኢትዮጵያ ማረጋገጥ አለብን ነው ያለችው፡፡
በነፃነት ሀሳብ የሚንሸራሸርባት ሰላም የሰፈነባት ኢትዮጵያ በልማትና በእድገት የዳበረች ኢትዮጵያንም እጠብቃለሁ ስትል ምኞቷን ገልፃለች።
በዓለምሰገድ አሳዬ