ቢዝነስ

የዓለም የምግብ ዋጋ በድጋሚ መጨመሩን ተመድ አስታወቀ

By Alemayehu Geremew

May 08, 2023

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም የምግብ ዋጋ በድጋሚ ጭማሬ ማሳየቱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ፡፡

የተመዱ የምግብ እና የእርሻ ድርጅት (ፋኦ) ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት በዓለም አቀፉ ገበያ በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ ሚያዝያ ወር ላይ በምግብ ሸቀጦች ላይ ጭማሪ ታይቷል።

በተለይ በወሩ በሩዝ ፣ በስኳር ምርት እና በስጋ ተዋፅዖዎች ላይ የዋጋ ጭማሪ መታየቱን ፋኦን ዋቢ አድርጎ አር ቲ ዘግቧል፡፡

በድርጅቱ ሪፖርት መሠረት ካሳለፍነው የፈረንጆቹ መጋቢት ወር አንፃር የስኳር ዋጋ አሁን ላይ በ17 ነጥብ 6 በመቶ ጨምሯል፡፡

ይህም ከፈረንጆቹ ጥቅምት 2011 ወዲህ በዋጋው ከፍተኛነት የመጀመሪያው ሆኖ ተመዝግቧል ነው ያለው፡፡

በሥጋ ዋጋ ላይ የታየው ጭማሪ የ1 ነጥብ 3 በመቶ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡

የስኳር ዋጋ ጭማሪው የተከሰተው ሕንድ እና ቻይና ከሚጠበቀው በታች የግብዓት ምርት ይኖራቸዋል የሚለውን ትንበያ ተከትሎ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም ታይላንድ እና የአውሮፓ ኅብረት ከሚጠበቀው በታች የስኳር አቅርቦት ይኖራቸዋል የሚለው መረጃ ለዋጋ ንረቱ የበኩሉን አስተዋፅዖ እንዳደረገም ተነግሯል፡፡

በሌላ በኩል በእህልና ጥራጥሬ ፣ በወተት ተዋፅዖ እና በአትክልት ዘይቶች ላይ አንፃራዊ የዋጋ ቅናሽ መታየቱ ተነግሯል፡፡

ከፈረንጆቹ መጋቢት ወር ጀምሮ ወተት እና የወተት ተዋፅዖዎች የ1 ነጥብ 7 በመቶ የዋጋ ቅናሽ ማሳየታቸው ሲመላከት በተለይ በአትክልት ዘይት ላይ እየታየ ያለው ቅናሽ ላለፉት አምሥት ተከታታይ ወራት በ1 ነጥብ 3 በመቶ መቀጠሉ ነው የተገለጸው፡፡