ኢትዮጵያና ማልታ በተለያዩ ዘርፎች በትብብር ለመስራት ተስማሙ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና ማልታ በአቪዬሽን ፣ ቱሪዝምና በዲፕሎማቲክ ስልጠና ዘርፎች በትብብር ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከማልታ ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይ እና የንግድ ሚኒስትር ኢያን ቦርግን ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም÷ በሁለትዮሽ እና በቀጠናዊ እንዲሁም በዓለም አቀፍ መድረክ ያላቸውን ትብብር ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማሸጋገር መክረዋል።
አቶ ደመቀ ÷ ማልታ ባለፉት ሁለት ዓመታት በዲፕሎማሲው ዘርፍ ለኢትዮጵያ ለሰጠችው ድጋፍና ባለፈው ዓመት ኤምባሲዋን በአዲስ አበባ በመክፈትያሳየችውን አጋርነት አድንቀዋል፡፡
ማልታ የተመድ የጸጥታው ም/ቤት ተለዋጭ አባል መሆኗን ያነሱት አቶ ደመቀ÷ በቆይታዋም የኢትዮጵያን እና የአፍሪካን ጥቅም ያስከበረ ስራ ለመስራት መዘጋጀቷን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢያን በርግ ማረጋገጣቸውን ጠቁመዋል።
ኢያን ቦርግ በበኩላቸው÷ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ቁልፍ ሚና ያላት ሀገር መሆኗን እና ለዚህም የመጀመሪያ ጉብኝታቸውን በአዲስ አበባ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ትግበራ አዎንታዊ መሆኑን ጠቅሰው÷የአውሮፓ ህብረትም ለኢትዮጵያ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት መናገራቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ከስምምነት መደረሱ የኢትዮጵያን እና ማልታን ትብብር ይበልጥ ስለማሳደግ መሰረት የጣለ መሆኑን አውስተዋል።
ስምምነቱም ማልታ በተለይም በአቪዬሽን ፣ ትምህርትና ዲፕሎማቲክ ስልጠና ዘርፎች ያላትን የተሻለ ተሞክሮ ለማጋራት መልካም እድል የሚፈጥር አጋጣሚ መሆኑን ጠቅሰዋል።