የሀገር ውስጥ ዜና

የፈረንሳይ ኤምባሲ ለአብዓላ ሆስፒታል የ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ አደረገ

By Amele Demsew

May 08, 2023

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የፈረንሳይ ኤምባሲ በዓፋር ክልል የሚገኘውን የአብዓላ ሆስፒታል መልሶ ለመገንባት የሚውል የ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ዩሮ የድጋፍ ስምምነት አድርጓል።

ስምምነቱ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ፣ በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ረሚ ማርሻክስ እንዲሁም የዓፋር ክልል ጤና ቢሮ ሓላፊ ያሲን ሓቢብ በተገኙበት ነው የተደረገው።

ኤምባሲው ከዚህ ቀደም ለደሴ ሆስፒታል መልሶ መቋቋም የ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ አድርጓል።

አምባሳደሩ እንደገለፁት ይህ ለሰላም ስምምነቱ መጠናከር ድጋፍ እንደሚያደርግ በመግለፅ በቀጣይ በትግራይ ክልል የዓድዋ ሆስፒታልን መልሶ ለመገንባት እንዲያስችል የ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ እንደሚደረግ ቃል ገብተዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው የድጋፍ ስምምነቱ በግጭቱ ለተጎዱ አካባቢዎች ለሁለተኛ ዙር የተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፥ ድጋፉ የመልሶ ግንባታውን በተሻለ ደረጃ ለማፋጠን እና ፈጣን ምላሽ ለመስጠት እንደሚያግዝ ገልፀዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ሓላፊ ሓሰን ሓቢብ እንዳሉት ÷በክልሉ ዞን ሁለት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ 24 የጤና ጣቢያዎች እንዲሁም ሁለት ሆስፒታሎች በግጭቱ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

የዛሬው ድጋፍ ከ300 ሺህ በላይ ዜጎች የሚገለገሉበትን የአብዓላ ሆስፒታልን መልሶ ለማቋቋም እንደሚያግዝ ነው የተናገሩት።

በታሪኩ ወልደሰንበት