Fana: At a Speed of Life!

ከ404 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች ተያዙ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የጉምሩክ ኮሚሽን ከሚያዝያ 20 እስከ 26 ቀን 2015 ዓ.ም ባደረገው ክትትል 404 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የገቢና የወጪ የኮንትሮባንድ እቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ተይዘዋል፡፡

ከተያዙት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል አልባሳት፣ ነዳጅ፣ የቁም እንስሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድሐኒት፣ ተሽከርካሪዎች፣ የመዋቢያ እቃዎች፣ የጦር መሳሪያዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ እጽ፣ የምግብ ዘይት እና የተለያዩ ሀገራት ገንዘቦች ይገኙበታል፡፡

በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ የወጪ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር የላቀ አፈጻጸም እንደተመዘገበም ኮሚሽኑ አስታውቋል።

በዚህም አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ፣ ጅግጅጋ እና ሞያሌ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች የላቀ አፈጻጸም ያስመዘገቡ ሲሆን÷ በቅደም ተከተላቸው 165 ሚሊየን፣ 35 ሚሊየን እና 22 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎችን በመያዝ ከፍተኛውን ድርሻ ወስደዋል ተብሏል፡፡

የጉምሩክ ኮሚሽን በዚህ የህግ ማስከበር ስራ ላይ ለተሳተፉ የኮሚሽኑ ሰራተኞች፣ የክልልና የፌደራል ፖሊስ አባላት እንዲሁም ለህዝቡ ምስጋና አቅርቧል፡፡

ድርጊቱን ለመግታትና በሀገር ኢኮኖሚ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽእኖ ለመከላከል ጉምሩክ ኮሚሽን ብቻ የሚያደርገው እንቅስቃሴ በቂ ባለመሆኑ ሁሉም ባላድርሻ አካላትና ህብረተሰቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አቅርቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.