ሩሲያ 78ኛውን የድል ቀን እያከበረች ነው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሲያ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ናዚ ጀርመንን ያሸነፈችበትን 78ኛ ዓመት የድል ቀን እያከበረች ነው፡፡
በሞስኮ ቀዩ አደባባይ እየተከበረ በሚገኘው የድል ቀን የቀደሞዋ ሶቪየት ህብረት አካል የነበሩ ሀገራት መሪዎችን ጨምሮ በርካታ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች ታድመዋል።
በድል ቀኑ ንግግር ያደረጉት የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፥ “ከወታደራዊ ሀይላችን በላይ አብልጠን የምንወደው ምንም ነገር የለም” ብለዋል፡፡
“ሩሲያ በዩክሬን ላይ የጀመረችው ዘመቻ ህልውናን የማረጋገጥ ጉዳይ” መሆኑን ጠቅሰው ዘመቻው ሩሲያ ሉዓላዊነቷን ለማስከበር የምታካሂደው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ዓለም የፖለቲካ ለውጥ ላይ ትገኛለች ያሉት ፕሬዚዳንቱ የሩሲያን ሀያልነት ለማስጠበቅ የወደፊት እጣ ፋንታን ለመወሰን ወታደራዊ ሀይላቸው በጀግንነት እየተዋጋ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ፑቲን “በእኛ ላይ ሊፈፅም የነበረውን ሽብርተኝነት አስወግደናል፤ የዶንባስ ነዋሪዎችን እንጠብቃለን፤ ደህንነታችንንም እናረጋግጣለን” ብለዋል በንግግራቸው።