Fana: At a Speed of Life!

ሲሳይ አውግቸው(ረ/ፕ) እና ጎበዜ ሲሳይን ጨምሮ ስድስት ግለሰቦች በተጠረጠሩበት የሽብር ወንጀል መነሻ ፍርድ ቤት ቀርቡ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሲሳይ አውግቸው (ረ/ፕ) እና ጎበዜ ሲሳይን ጨምሮ ስድስት ግለሰቦች በተጠረጠሩበት የሽብር ወንጀል መነሻ ፍርድ ቤት ቀርቡ።

ተጠርጣሪዎቹ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1 ኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርበው ክርክር ተደርጓል።

ተጠርጣሪዎቹ ሲሳይ አውግቸው(ረ/ፕ)፣ ማዕረጉ ቢያብን(ፕ/ር) ፣ሰለሞን ልመንህ፣ ሄኖክ አዲስ፣ ነዋይ ዩሃንስ እና ጎበዜ ሲሳይ ናቸው።

መርማሪ ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ ህገ መግስቱን እና ህገመንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለማፍረስ ፣የፖለቲካ አላማን ለማሳካት፣ ኢ- መደበኛ አደረጃጀት በመፍጠር የወታደራዊ ስልጠና ክንፍ እና የሚዲያ ፕሮፖጋንዳ ክንፍ በማዋቀር የሽብር ወንጀል ድርጊት ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ ነበር በማለት የጥርጣሬ መነሻ ነጥቦችን ዘርዝሮ ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ አቅርቧል።

በዚህ መልኩ ከተጠረጠሩበት የሽብር ወንጀል መነሻ ላይ ተጨማሪ ማስረጃ አሰባስቦ ለመቅረብ የ14 ቀን የማጣሪያ ጊዜ እንዲሰጠው ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች በበኩላቸው÷” ፖሊስ ከዚህ በፊት ሁከትና ብጥብጥ ወንጀል በሚል ተጠርጣሪዎችን ለመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አቅርቦ በነበረበት ወቅት ባቀረበው መልኩ ተመሳሳይ ይዘት ያለው የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ምክንያት ነው ያቀረበው ” ሲሉ ተከራክረዋል።

በተጨማሪም ጎበዜ ሲሳይን በሚመለከት የተጠረጠረው በሙያው ተፈጽሟል በተባለ ወንጀል በመሆኑ ጉዳዩ ሊታይ የሚገባው በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ነው ሲሉም ተከራክረዋል።

መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ ከዚህ በፊት በሁከትና ብጥብጥ ወንጀል ተጠርጥረው ምርመራ ሲደረግባቸው በነበረበት ወቅት ለሽብር ወንጀል የሚያስጠረጥሩ ማስረጃዎች በመገኘታቸው ምክንያት ዛሬ በሽብር ወንጀል መዝገብ እንዲቀርቡ መደረጉን አብራርቷል።

ጎበዜ ሲሳይን በሚመለከት የተጠረጠረው በሽብር ወንጀል ተግባር ላይ ያለውን ተሳትፎ የሚያመላክት የጥርጣሬ መነሻ ማስረጃ በማግኘታችን ምክንያት ነው በማለት ፖሊስ መልስ ሰጥቷል።

ተጠርጣሪዎቹ በዋስ ቢወጡ ማስረጃ እና ግብረ አበር ሊያሸሹብን ይችላሉ ሲል ስጋቱን ገልጾ ፖሊስ የዋስትና ጥያቄያቸውን ተቃውሟል።

የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ መርምሮ ተገቢውን ትዕዛዝ ለመስጠት ለነገ ከሰዓት በይደር ቀጥሯል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.