Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካ አቪዬሽን ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አህጉራዊ የአቪዬሽን ጉባኤ “የአፍሪካ የተቀናጀ የአየር ትራንስፖርት ገበያን በፍጥነት ማስተግበር” በሚል መሪ ሃሳብ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት መካሄድ ጀመረ።

የአፍሪካ ሲቪል አቪዬሽን ኮሚሽን ዋና ጸሃፊ አዲፉንኬ አዲዬሚ በአፍሪካ የተቀናጀ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ፕሮጀክት የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 አካል መሆኑን በመድረኩ አስታውሰዋል።

ፕሮጀክቱን እውን በማድረግ ሂደት ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አቪዬሽን እድገት እያበረከተች ያለው አስተዋጽኦ ምስጋና የሚገባው ነው ብለዋል።

በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ 35 የአፍሪካ ሀገራት የቀጥታ በረራ ማድረጉ በራሱ ግዙፍ አስተዋጽኦ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ፕሮጀክቱ አፍሪካ ለምታልመው ጠንካራ ምጣኔ ሀብታዊ ጥምረት እውን መሆን ትልቅ እገዛ ስለሚኖረው ለተግባራዊነቱ በትብብር መስራት እንደሚገባም ተመላክቷል፡፡

የፕሮጀክቱ ምሉዕ ተግባራዊነትተጨማሪ 15 ነጥብ 9 ሚሊየን ሰዎችን ለማጓጓዝ፣ ለ597 ሺህ ሰዎች የስራ እድል መፍጠር እና የ4 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር ጥቅል አመታዊ እድገት ምክንያት እንደሚሆን ተገልጿል።

በአፍሪካ አንድ የተቀናጀ የአየር ትራንስፖርት እንዲተገበር ኢትዮጵያን ጨምሮ 36 የአፍሪካ ሀገራት የገበያው አካል ለመሆን ፊርማቸውን አኑረዋል።

ሀገራቱ 80 በመቶ የአፍሪካ አቪዬሽን ገበያን የሚይዙ ናቸው ተብሏል።

በበርናባስ ተስፋዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.