ሩሲያ ላይ በተጣለው ማዕቀብ ቻይና እና ጀርመን መምከራቸው ተሰማ
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 2 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሲያ ላይ በተጣለው የንግድ ማዕቀብ ላይ ቻይና ከጀርመን ጋር መምከሯ ተገለጸ፡፡
የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኪን ጋንግ ከጀርመን አቻቸው አናሌና ቤርቦክ ጋር ጠንካራ ፣ ግልጽ እና አወንታዊ ውይይት ማድረጋቸውን ሲ ጂ ቲ ኤን ዘግቧል፡፡
ሁለቱ ሚኒስትሮች በጀርመኗ መዲና በርሊን ባካሄዱት ውይይት የዩክሬንን ወቅታዊ ጉዳይ እና ዓለምአቀፉን የዓየር ንብረት ለውጥ በተጨማሪ አጀንዳነት አንስተው መምከራቸው ተነግሯል፡፡
ሚኒስትሮቹ የአውሮፓ ኅብረት በሥምንት የቻይና ኩባንያዎች ላይ ሊጥል ባዘጋጀው ማዕቀብ ላይም መነጋገራቸው ተገልጿል፡፡
የአውሮፓ ኅብረት ኩባንያዎቹ ላይ የንግድ ማዕቀብ ሊጥል እየተዘጋጀ ያለው ሩሲያ ለምታመርታቸው የጦር መሣሪያዎች ግብዓት የሚሆኑ ቁሶችን እያመረቱ ይልካሉ በሚል ነው፡፡
የጀርመኗ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ ÷ ሩሲያ ላይ በሚጣለው ማዕቀብ ጉዳይ ላይ ኅብረቱ ዩክሬንን ከጥቃት ለመከላከል የተለየ አማራጭ እየፈለገ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
ኪን ጋንግ በበኩላቸው ÷ ቻይና በግጭት ውስጥ ለሚገኙት ሀገራትም ሆነ ለቀጣናው የጦር መሣሪያ የማቅረብም ሆነ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት እንደሌላት አቋማቸውን በድጋሚ ግልፅ አድርገዋል፡፡
በመጨረሻም የቻይና እና የሩሲያ ኩባንያዎች ÷ የአውሮፓ ኅብረት በሥጋትነት ካነሳው ሽርክና በተለየ መልኩ መደበኛ የሆነ የንግድ ልውውጥ እና ትብብር እንዳላቸው በዚህም ላይ የማንንም ጣልቃ ገብነት እንደማይቀበሉ ግልጽ አድርገዋል።