በኦሮሚያ ክልል በድርቅ ለተጎዱ ዞኖች ከ26 ቢሊየን ብር በላይ ድጋፍ ተደርጓል
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል በዘንድሮው ዓመት በድርቅ ለተጎዱ 10 ዞኖች ከ26 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት የአይነትና የተለያየ ድጋፍ መደረጉን የክልሉ ቡሳ ጎኖፋ ተቋም ገለጸ።
ድጋፉ ከፌዴራልና ከክልሉ መንግሥት፣ መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት እንዲሁም ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና ከክልሉ ሕዝብ የተገኘ መሆኑ ተገልጿል።
የተቋሙ ሃላፊ ሃብታሙ ሲሳይ÷በዘንድሮው ዓመት በ10 የክልሉ ዞኖች የተከሰተውን ድርቅ በራስ አቅም ለመቋቋም ሲሰራ መቆየቱንም ተናግረዋል።
በተለይም በቦረና፣ ጉጂ፣ ምስራቅ ባሌ፣ ምዕራብና ምስራቅ ሐረርጌ ዞኖች ድርቁ በሰውና በእንስሳት ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል የተሻለ አቅም የተገነባበት ዓመት ነው ብለዋል ።
በተጨማሪም በድርቁ በተጎዱ አካባቢዎች ያሉ ተማሪዎችም በምግብ እጥረት ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው እንዳይቀሩ ቡሳ ጎኖፋ የማይተካ ሚና መጫወቱን ገልጸዋል።
በዚህም በአሁኑ ወቅት በክልሉ ከ5 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ የተማሪዎች ምገባ እየተከናወነ መሆኑን ነው ያብራሩት፡፡
በአሁኑ ወቅት ከ2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ግምት ያለው ሃብት በጥሬ ገንዘብና በአይነት መሰብሰብ መቻሉን ጠቅሰው÷እስከ መጪው ሰኔ ድረስ የሃብት አሰባሰቡን 3 ቢሊየን ብር ለማድረስ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በዚህም በመጪው ዓመት በሁሉም ትምህርት ቤቶች የምገባ መረሐ ግብር ለማስኬድ ታቅዶ ሀብት የማሰባሰቡ ስራ ተጠናክሮ እንደቀጠለ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡