የሀገር ውስጥ ዜና

አቶ ኦርዲን በድሪ በኢትዮጵያ የካናዳ አምባሳደር ስቴፋን ጆቢን ጋር ተወያዩ

By Alemayehu Geremew

May 10, 2023

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 2 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በኢትዮጵያ የካናዳ አምባሳደር ስቴፋን ጆቢን ጋር ተወያይተዋል።

አቶ ኦርዲን ÷አምባሳደር ስቴፋን ጆቢን እና ልዑካቸው የሠላም፣ የመቻቻልና የአብሮነት ከተማ የሆነችውን የሐረር ከተማ በመጎብኘታቸው ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ርዕሠ-መሥተዳድሩ ÷ ሐረር ከተማ የጁገል ዓለም አቀፍ ቅርስን ጨምሮ በዩኔስኮ የተመዘገቡ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ቅርሶች መገኛ መሆኗን አውስተዋል፡፡

የተለያዩ ባሕል እና ዕምነት ያላቸው ሕዝቦች በሠላም፣ በፍቅርና በመቻቻል የሚኖሩባት ከተማ ስለመሆኗም ማስረዳታቸውንም የሐረሪ ክልል ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመለክታል፡፡

በውይይታቸውም በመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ በቱሪዝም እንዲሁም ታሪካዊ ቅርሶችንና ሙዚዬሞችን በመጠበቅ ረገድ በትብብር ለመሥራት መስማማታቸው ተገልጿል፡፡