አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በዓም አቀፉ የፌዴሬሽኖች መድረክ ተሳተፉ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በዓለም አቀፉ የፌዴሬሽኖች መድረክ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ተሳትፈዋል።
በስዊዘርላንድ ኦራው በተካሄደው ዓለም አቀፉ የፌዴሬሽኖች መድረክ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ የተሳተፉት አምባሳደሯ ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን ልምድ ለተሳታፊዎች አጋርተዋል።
በኮቪድ ወቅት የፌደራሊዝም ስርዓት በኢትዮጵያ የነበረውን አተገባበር እና የፌደራል መንግስቱ ከክልሎች ጋር የነበረውን ሁለንተናዊ ቅንጅት መነሻ በማድረግ የሀገሪቱን ተሞክሮ አቅርበዋል።
በመድረኩ ከኢትዮጵያ ባሻገር የጀርመን እና ብራዚል ተወካዮችም ሀገራቱ በዘርፉ ያላቸውን መልካም ተሞክሮ አቅርበዋል።
ዓለም አቀፉ የፌዴሬሽኖች መድረክ በዛሬው ውሎ ያለፈውን ዓመት የስራ ክንውን አፈፃፀም የገመገመ ሲሆን በቀጣይ መድረኩን ይበልጥ ሊያጠናክሩ በሚችሉ ስድስት አጀንዳዎች ላይ ውይይት በማካሄድ አቅጣጫ አስቀምጧል።
የመድረኩ ተካፋዮች ከስብሰባው ጎን ለጎንም በሰሜናዊ ስዊዘርላንድ በምትገኘው የኦራው ከተማ ፓርላማ በመገኘት ጉብኝት አካሂደዋል።
የፌዴሬሽን መድረክ በፌዴራሊዝምና ባልተማከለ አስተዳደር አተገባበር ላይ ንፅፅራዊ እውቀት የማበልፀግና የተሻለ ልምድን በዓለም አቀፍ የትስስር መረብ በኩል ለማጋራት በማለም የተመሰረተ ዓለም አቀፍ ድርጅት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡