አምስት የፌዴራል ተቋማት ስማርት ኮሙኒኬሽን ክፍሎች ተመረቁ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአምስት የፌደራል ተቋማት የተገነቡ የስማርት ኮሚኒኬሽን ክፍሎች እና ስርዓት ተመርቆ ስራ ጀመረ።
በዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስተባባሪነት የተገነቡ ስማርት ክፍሎቹ ዘመኑ ያፈራውን ቴክኖሎጂ የሚጠቀሙና ለቀላልና ቀልጣፋ የስራ ግንኙት የሚያግዙ ናቸው ተብሎላቸዋል።
በየተቋማቱ የተገነቡት ክፍሎቹ ዘመናዊ ስማርት ስክሪን፣ ስማርት ላይቲንግ፣ የተሻሻሉ የቴሌ እና የቪዲዮ ኮንፈረንሶችን ማድረግ የሚያስችሉ ስማርት መሳሪያዎች፣ ምቹ ክፍሎች፣ የአየር ማቀዝቀዣ፣ የድምፅ ብክለትን የሚቀንሱ መሳሪያዎችና የኔትወርክ ማሳሪያዎች የተገጠሙላቸው ናቸው።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ፥ የስማርት ኮሙኒኬሽን ክፍሎቹና ፕላትፎርሙ ስራ መጀመር ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በሚሰራው ስራ ውስጥ የራሱን አስተዋፅኦ ያደርጋል ብለዋል።
በቀጣይ በሁሉም የክልል ፕሬዚዳንት ቢሮዎች እንዲሁም በተመረጡ የፌደራል ተቋማት 20 ስማርት ኮሙኒኬሽን ክፍሎች የመገንባት ስራ ይቀጥላልም ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታዋ፡፡
ስርዓቱ በአካል መገናኘትን በማስቀረት የተቀላጠፈ ስራ ለመስራት፣ ስልጠናና ስብሰባዎችን ለማካሄድና ስምሪትን ለመስጠት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
በምዕራፍ አንድ የተገነቡት ለኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ ለገንዘብ ሚኒስቴር፣ በትምህርት ሚኒስቴር ለኢትዮጵያ ትምህርትና ምርምር ኔትዎርክ፣ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ለዲጂታል መታወቂያና ለኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን ናቸው፡፡
በምዕራፍ ሁለት ደግሞ ለ20 ተቋማት እንደሚገነቡ ተገልጿል።
የስማርት ኮሙኒኬሽን ክፍሎቹ በአምስቱም ተቋማት በኦንላይን በተመሳሳይ ሰዓት ተመርቀው ወደ ስራ ገብተዋል።