Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ እና ፓኪስታን በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዘርፍ በጋራ ለመስራት ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)ኢትዮጵያ እና ፓኪስታን በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዘርፍ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።

ስምምነቱን ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና የፓኪስታን ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ተፈራርመዋል፡፡

በፓኪስታን ኢዝላማባድ በተከናወነው የፊርማ ስነስርዓት ላይ እንደተገለፀው ስምምነቱ ሁለቱ ሀገራት በመስኩ ያላቸውን ተሞክሮ የሚለዋወጡበት እና አቅማቸውን የሚያጎለብቱበት ነው።

በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በሚኒስትር ዲኤታ ማዕረግ አማካሪ ፎዚያ አሚን (ዶ/ር) ስምምነቱ የሁለቱ ሀገራት የሳይንስ እና የፈጠራ ተቋማት አብረው የሚሰሩበትን መደላድል ይፈጥራል ብለዋል።

ከስምምነቱ አብይ ትኩረቶች አንዱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና የኢንዱስትሪዎች ትስስርን ለማጎልበት የሚሰሩ ስራዎችን ማሳደግ እንደሆነም ገልፀዋል ።

ፓኪስታን ይበልጥ በጨርቃጨርቅ እና ፋርማሲውቲካል ዘርፎች ከፈጠረችው አቅም ኢትዮጵያ ልምድ የምትቀስምበትን ዕድል ስምምነቱ እንደሚፈጥርም ሚኒስትር ዴኤታዋ ጨምረው ገልፀዋል።

የፓኪስታን ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ዋና አማካሪ ዘይኑል አበዲን ስምምነቱ በኢትዮጵያ እና ፓኪስታን መካከል አዲስ የትብብር መስክ የሚፈጥር መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ይህም ሀገራቱ በሳይንስ ምርምር እና ቴክኖሎጂ ፈጠራ የፈጠሩትን አቅም እንዲያጎለብቱ እና የእውቀት ሽግግር እንዲኖር መሰረት የሚጥል ነው ብለዋል።

በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ አፈፃፀም ለመግባት ሚኒስቴሩ ዝግጅት ማድረጉ መገለፁን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.