Fana: At a Speed of Life!

ሰላምና ብልጽግናን ማሳካት የሚያስችሉ የጸጥታና ደህንነት ተቋማት ተገንብተዋል – ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል

 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ሰላምና ደህንነትን በማረጋገጥ የታሰበውን ብልጽግና ማሳካት የሚያስችሉ የጸጥታና ደህንነት ተቋማት መገንባታቸውን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያን የአምስት ዓመት የለውጥና የስኬት ጉዞ የሚዘክር መርሐ-ግብር ተከናውኗል።

ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ÷መርሐግብሩ በኢትዮጵያ አራቱም ማዕዘናት ለሀገራቸው ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ ከመከላከያ ሰራዊት ጋር በመተባበር እስከ ህይወት መስዋዕትነት የከፈሉ የፖሊስ አባላት የሚመሰገኑበት ነው።

የፌዴራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ የወንጀል ስጋትን ቀድሞ በማምከን ከተከሰተ በኋላም ወንጀለኞችን ተከታትሎ ለህግ በማቅረብ ህዝብ የጣለበትን ኃላፊነት በብቃት እየተወጣ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋትን በማምጣት የታሰበውን ብልጽግና ማሳካት የሚያስችሉ የጸጥታና የደህንነት ተቋማት መገንባታቸውንም ተናግረዋል፡፡

ከለውጡ በፊት የፌዴራል ፖሊስ በህዝብ ዘንድ የነበረው አመኔታ ዝቅ ያለ እንደነበር ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት በፖሊስ ተቋማት ላይ በተሰራው ሁሉን አቀፍ የሪፎርም ስራ ፖሊሳዊ ሚናውን በአግባቡ መወጣት የሚችል ሰራዊት መገንባቱን ገልጸዋል።

በዚህም የፖሊስ ሰራዊቱ ለህዝብ ደህንነትና ሰላም መረጋገጥ ኃላፊነቱን በብቃት መወጣት የሚያስችል አስተማማኝ ቁመና እንዲኖረው መደረጉን ነው ያነሱት።

በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ በበኩላቸው ÷ ሰራዊቱ ባለፋት ሶስት ዓመታት የተከሰቱ የሰላም ችግሮችን ለመፍታት ጠንካራ አደረጃጀት በመፍጠር ህዝብና መንግሥት የሰጡትን ተልዕኮ በብቃት እየተወጣ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በቀጣይም ሀገር ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱ ጸረ ሰላም ኃይሎችን የመዋጋትና የወንጀል ስጋቶችን የማምከን ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ማረጋገጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.