የእንቅስቃሴ ገደቦችን ማንሳት የኮሮና ቫይረስ እንዲያገረሽ ያደርጋል- የአለም ጤና ድርጅት
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 15፣ 2012(ኤፍ ቢ ሲ) ሀገራት የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመግታት የጣሏቸውን የእንቅስቃሴ ገደቦችን ማንሳታቸው የቫይረሱ ስርጭት እንዲያገረሽ ያደርጋል ሲል የአለም ጤና ድርጅት አስጠነቀቀ።
የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም በመግለጫቸው የአለም መንግስታት የኮሮና ቫይረስ እንዳይስፋፋ ለመቆጣጠርና ለመከላከል ያወጡትን ከቤት ያለመውጣት ገደብ አሁን ላይ ማንሳታቸው ቫይረሱ እንዲባባስ ያደርጋል ብለዋል።
በአፍሪካ፣ በምስራቅ አውሮፓ ፣ በማዕከላዊና ደቡብ አሜሪካ በኮሮና ቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከፍ ሊል እንደሚችል ዋና ዳይሬክተሩ አስጠንቅቀዋል፡፡
“ስህተት መስራት የለብንም፤ ቫይረሱ ለረጅም ጊዜ ከእኛ ጋር ይቆያል” ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፥ ኮሮና ቫይረስን ለመቆጣጠርና ለመከላከል ቸልተኝነት ማሳየት አይገባም ብለዋል።
በመግለጫቸው በምዕራብ አውሮፓ ወረርሽኙ መረጋጋትና መቀነስ ቢያሳይም በብዙ ሃገራት ወረርሽኙ ጅማሬ ላይ መሆኑን ነው የጠቆሙት።
በወረርሽኙ ቫይረሱ ዘግይቶ የገባባቸው ሃገራት በአሁኑ ወቅት ቫይረሱ እየተስፋፋባቸው መምጣቱንም ገልፀዋል።
በተጨማሪም ቤት መቆየት እና ርቀትን መጠበቅ ቫይረሱን ለመቆጣጠርና ለመከላከል የሚረዳ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም ብለዋል።
ምንጭ፦ ቢቢሲ