በአማራ ክልል ከኦፓልና ወርቅ ማዕድናት 7 ነጥብ 9 ሚሊየን ዶላር ገቢ ተገኘ
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 5 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን የወረኢሉ የኦፓል ማዕድን ምርት ለገበያ መቅረብ ጀምሯል፡፡
በአማራ ክለል በተለያዩ አካባቢዎች በአምስት ዘርፍ የሚከፈሉ 40 የማዕድን ሃብት አይነቶች መኖራቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡
ይሁን እንጂ ሃብቱ ገና ያልተነካ በመሆኑ በአግባቡ አልምቶ መጠቀም እንደሚገባ ነው ጽህፈት ቤቱ ያስገነዘበው፡፡
አሁን ላይ በክልሉ ከፍተኛ የማዕድን ሃብት ክምችት ይገኝባቸዋል ተብለው በተለዩ አካባቢዎች እየተሰራ ባለው ስራም አበረታች ውጤት እየተመዘገበ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡
ክልሉ ለመጀመሪያ ጊዜ በበጀት ዓመቱ 85 ነጥብ 4 ኪ.ግ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ገቢ ያደረገ ሲሆን÷ከኦፓልና ወርቅ ማዕድናትም 7 ነጥብ 9 ሚሊየን ዶላር ገቢ ማግኘቱ ተገልጿል፡፡
በክልሉ ከፍተኛ የማዕድን ሃብት ክምችት ይገኝባቸዋል ተብለው ከተለዩ አካባቢዎች መካከል የደቡብ ወሎ ዞን ቀዳሚውን ስፍራ እንደሚይዝ ተጠቅሷል፡፡
ለአብነትም ነዳጅ፣ ኦፓልና የድንጋይ ከሰልን ጨምሮ ሌሎች የማዕድን ሃብት አይነቶች እንደሚገኙበት ነው የተመላከተው።
በወረዳው በሁለት የማዕድን አፈላላጊ ማኀበራት በተደራጁ ወጣቶች አማካኝነት የተመረተው የኦፓል ማዕድንም ለገበያ መቅረብ መጀመሩን የጽ/ቤቱ መረጃ ያመላክታል፡፡