Fana: At a Speed of Life!

በአፍሪካ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ25 ሺህ በለጠ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 15፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአፍሪካ አህጉር በኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) የተያዙ ሰዎች ቁጥር 25 ሺህ 940 መድረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።

በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ2 ሚሊየን 630 ሺህ መብለጡን የሚያሳየው የጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ፤ ከእነዚህም ውስጥ 25 ሺህ 940 ያህሉ በአፍሪካ አህጉር የሚገኙ ናቸው።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በቫይረሱ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር ከ183 ሺህ ሲበልጥ፤ በአፍሪካም በኮቪድ-19 ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር ከ1 ሺህ 200 ተሻግሯል።

በአፍርካ ከ6 ሺህ 900 በላይ ሰዎች ደግሞ ከወረርሽኙ ማገገማቸውንም የዩኒቨርሲቲው መረጃ የሚያመላክት ሲሆን፥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ከ714 ሺህ በላይ ሰዎች አገግመዋል።

በደቡብ አፍሪካ 3 ሺህ 635 ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን፥ በሀገሪቱ በኮሮናቫይረስ ከተያዙት ውስጥ የ65 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ፤ 1 ሺህ ሰዎች ማገገማቸውም ነው የተገለፀው።

ግብፅበ እስካሁን ባለው መረጃ መሰረት 3 ሺህ 659 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን፥ ከእነዚህም 935 ሲያገግሙ፤ 276 ሰዎች ህይወታቸው አልፏል።

በአልጄሪያም 2 ሺህ 910 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ፥ 402 ሰዎች ህይወታቸው አልፎ፤ 1 ሺህ 204 ሰዎች ደግሞ አገግመዋል።

ወደ ምስራቅ አፍሪካ ስንመጣ ኬንያ 303 ሰዎች በቫይረሱ እንደተያዙ ያስታወቀች ሲሆን፥ ከእነዚህም 83 ሰዎች ሲያገግሙ፤ 14 ሰዎች ደግሞ ህይወታቸው አልፏል።

በጂቡቲ 974 ሰዎች፣ በኤርትራ 39 ሰዎች፣ በሶማሊያ 286 ሰዎች፣ ሱዳን 162 ሰዎች እንዲሁም ደቡብ ሱዳን 4 በቫይረሱ መያዛቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በኢትዮጵያም እስከ ትናንትናው እለት ባለው መረጃ በአጠቃላይ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 116 የደረሰ ሲሆን፥ ከእነዚህም 21 ሲያገግሙ፤ 3 ሰዎች ደግሞ ህይወታቸው አልፏል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.