በቱርክ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አሸናፊውን ለመለየት 2ኛ ዙር ድምጽ እንደሚሠጥ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የቱርክ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተፎካካሪዎች አብላጫ ድምጽ ባለማግኘታቸው ወደ 2ኛ ዙር ድምጽ የመስጠት ሂደት ተሸጋግሯል።
እስካሁን ባለው ሂደት የወቅቱ የሀገሪቷ ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ታይፕ ኤርዶኻን 49 ነጥብ 37 በመቶ ድምፅ አግኝተዋል፡፡
የእርሳቸው ዋነኛ ተቀናቃኝ ሆነው የቀረቡት ኪሊዳሮግሉ በጠባብ የድምፅ ልዩነት 44 ነጥብ 99 በመቶ የሚሆነውን የቱርካውያን መራጮች ድምፅ አግኝተዋል ነው የተባለው፡፡
ተፎካካሪዎች ከ50 በመቶ በላይ የማስተማመኛ ድምፅ አለማግኘታቸውን ተከትሎም አሸናፊውን ለመለየት ወደ ሁለተኛ ዙር ድምፅ የመሥጠት ሂደት መሸጋገሩን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
ፕሬዚዳንት ኤርዶኻንም በመጀመሪያው የድምፅ ቆጠራ 50 በመቶ የመተማመኛ ድምፅ ማግኘት ባይችሉም መሪ ሆነው ወደ ሁለተኛ ዙር ድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ተሸጋግረዋል ነው የተባለው።
በቱርክ ለሚቀጥሉት አምሥት ዓመታት ሕዝብ ያገለግሉኛል ያላቸውን ፕሬዚዳንት እና የፓርላማ አባላት ለመምረጥ ከ64 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ ሰዎች ተመዝግበው ድምፅ ሰጥተዋል፡፡