Fana: At a Speed of Life!

የአርቲስት ሂሩት በቀለ አስከሬን ሽኝት መርሐ ግብር በሀገር ፍቅር ቴአትር ተከናወነ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአርቲስት ሂሩት በቀለ አስከሬን ሽኝት መርሐ ግብር በሀገር ፍቅር ቴአትር ተከናውኗል፡፡

መስከረም 28 1935 ዓ/ም የተወለደችው ሂሩት ከ1950 ዎቹ መጀመሪያ እስከ 1980ዎቹ መጨረሻ ድረስ በርካታ የሙዚቃ ስራዎችን ለአድማጭ አበርክታለች።

ከዳህላክ፣ ዳሽን እና ዋልያዎች ባንድ ጋር በርካታ ስራዎችን የሰራቸው አርቲስቷ ፥ ለ35 ዓመታት ያክል በፖሊስ ሠራዊት የሙዚቃና ቴአትር ክፍል ነበር ያገለገለችው።

በእነዚህ 35 ዓመታትም ከ200 በላይ ሙዚቃዎችን አበርክታለች።

ከ38 ሙዚቃዎች በላይ በሸክላ እንዲሁም ከ14 አልበሞች በላይ በካሴት መታተማቸው የታሪክ ማህደሯ ያስረዳል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ ከውጪም ከሀገር ውስጥም የተለያዩ ከፍተኛ ሽልማት ተበርክቶላታል።

ከ1987 ጀምሮ ለ25 ዓመታት በላይ በቤተ ክርስቲያን ስታገለግል ሦስት የመዝሙር አልበሞችን አበርክታለች።

በአዲስ አበባ ከተማ ተወልዳ ያደገችው ሂሩት የሠባት ልጆች እናት፣ የ10 ልጆች አያትና የሠባት ልጆች ቅድመ አያት ነበረች።

በሽኝቱ መርሀ ግብሩም ከኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስትያናት ህብረት ፓስተር ታምራት ሃይሌን ጨምሮ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አባላትና አመራሮች፣ ከአዲስ አበባ ከንቲባ ፅህፈት ቤት፣ አንጋፋ አርቲስቶችና የቀድሞ የሙያ አጋሮቿ እንዲሁም አድናቂዎቿ ተገኝተዋል።

ባለፈው ሣምንት በ80 ዓመቷ ህልፈተ ህይወቷ የተሰማው አርቲስት ሂሩት በቀለ የቀብር ስነ ስርዓት በዛሬው ዕለት ከቀኑ 7 ሰዓት በጴጥሮስ ወ ጳውሎስ ይፈፀማል።

በታሪኩ ወ/ሠንበት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.