ዓለምአቀፋዊ ዜና

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በቻይና የስራ ጉብኝት እያደረጉ ነው

By Mikias Ayele

May 15, 2023

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በቻይና ይፋዊ የስራ ጉብኝት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

ፕሬዚዳንቱ ትናንት ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ቤጂንግ የገቡ ሲሆን÷በቆይታቸውም ከቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ችያንግ ጋር በሀገራቱ የጋራ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ችያንግ ÷ኤርትራ እና ቻይና ያላቸውን ስትራቴጂካዊ ትብብር ይበልጥ ማጠናከር እንዳለባቸው አንስተዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በበኩላቸው ÷ አፍሪካን ጨምሮ የተለያዩ የዓለም ሀገራት የቻይናን ፖለቲካዊ አስተዋፅኦ አጥብቀው ይፈልጋሉ ብለዋል፡፡

ቻይና በአፍሪካ ቀንድ ያላትን ይዞታ ለማጠናከር እንዲሁም ከስዊዝ ካናል፣ ከባህረ ሰላጤው ሀገራት እና ከሰሜን አውሮፓ ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ኤርትራ ለቤጂንግ ቁልፍ የጂኦፖለቲካል ቦታ እንደሆነች ይነገራል፡፡

በሌላ በኩል ኤርትራ በጅቡቲ ለሰፈራው የቻና ጦር ጎረቤት ሀገር መሆኗ ቻይና ፍትሃዊ የዓለም ስርዓትን ለማስፍን የምታደርገውን እንቅስቃሴ ያግዛል መባሉን ሬውተርስ ዘግቧል፡፡