የአርቲስት ሂሩት በቀለ የቀብር ሥነ-ሥርዓት ተፈጸመ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአርቲስት ሂሩት በቀለ የቀብር ሥነ-ሥርዓት ተፈጽሟል፡፡
መስከረም 28 ቀን 1935 ዓ.ም የተወለደችው ሂሩት ከ1950 ዎቹ መጀመሪያ እስከ 1980ዎቹ መጨረሻ ድረስ በርካታ የሙዚቃ ስራዎችን ለአድማጭ አበርክታለች።
ከዳህላክ፣ ዳሽን እና ዋልያዎች ባንድ ጋር በርካታ ስራዎችን የሰራቸው አርቲስቷ ፥ ለ35 ዓመታት ያክል በፖሊስ ሠራዊት የሙዚቃና ቴአተር ክፍል ነበር ያገለገለችው።
በእነዚህ 35 ዓመታትም ከ200 በላይ ሙዚቃዎችን አበርክታለች።
ከ38 ሙዚቃዎች በላይ በሸክላ እንዲሁም ከ14 አልበሞች በላይ በካሴት መታተማቸው የታሪክ ማህደሯ ያስረዳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ ከውጪም ከሀገር ውስጥም የተለያዩ ከፍተኛ ሽልማቶች ተበርክቶላታል።
ከ1987 ጀምሮ ለ25 ዓመታት በላይ በቤተ ክርስቲያን ስታገለግል ሦስት የመዝሙር አልበሞችን አበርክታለች።
በአዲስ አበባ ከተማ ተወልዳ ያደገችው ሂሩት በቀለ የሠባት ልጆች እናት፣ የ10 ልጆች አያትና የሠባት ልጆች ቅድመ አያት ነበረች።
ባለፈው ሣምንት በ80 ዓመቷ ህልፈተ ህይወቷ የተሰማው አርቲስት ሂሩት በቀለ የቀብር ሥነ-ሥርዓት በዛሬው ዕለት በጴጥሮስ ወ ጳውሎስ ተፈጽሟል፡፡