Fana: At a Speed of Life!

የቻይና መንግስት በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል ያጓጓዝውን የኮሮናቫይረስ መከላከያ ግብአቶች ለአፍሪካ ሀገራት አስረከበ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 15፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የቻይና መንግስት በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል ያጓጓዝውን የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ግብአቶች ለአፍሪካ ሀገራት አስረከበ።

የርክክብ ስነ ስርአቱ በዛሬው እለት በኢትዮጵያ አየር መንገድ የካርጎ አገልግሎት ተፈጽሟል።

በስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ታን ጂ ያን እንደተናገሩት፥ ቻይና በፈተና ወቅት ከጎኗ ለነበሩ የአፍሪካ ሀገራት የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።

አምባሳደሩ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በካርጎ አገልግሎቱ ለመላው አለም እያበረከተ ለሚገኘው የማይተካ ሚና ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም፥ ቻይና ለአፍሪካ ሀገራት አስፈላጊውን ድጋፍ በአስፈላጊው ጊዜ አድርጋለች ብለዋል።

“በኮቪድ 19 መከላከል ላይ የምናደርገውን የካርጎ አገልግሎት አጠናክረን እንቀጥላለን” ያሉት ዋና ስራ አስፍጻሚው፥ “ሁሉም የአፍሪካ ሀገራት በመተባበር እና በጋራ በመስራት ቫይረሱን ሊዋጉት ይገባልም” ነው ያሉት።

አየር መንገዱ ከጃክማ ፋውንዴሽን ለአፍሪካ ሀገራት የተላኩ ቁሳቁሶችን ለ51 ሀገራት በ6 ቀናት ማድረሱን በማንሳት፥ በጥንቃቄ እና ፍጥነት ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አቶ ተወልደ ተናግረዋል።

ቻይና ዛሬ ያበረከተቸው ድጋፍ ለ12 አፍሪካ ሃገራት የተበረከተ ነው።

ሀገራቱም አንጎላ፣ ካሜሮን፣ ማእከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ቻድ፣ ጅቡቲ፣ ሌሴቶ፣ ማዳጋስካር፣ ናሚቢያ፣ ኒጀር፣ ሩዋንዳ፣ ሶማሊያ እና ዛንዚባር ናቸው።

ኢትዮጵያ ቀደም ብሎ ከቻይና መንግስት ቫይረሱን ለመከላከል የሚያስችሉ ቁሳቁሶች ድጋፍ ማግኘቷ ይታወሳል።

ከቀናት በፊትም የቻይና የህክምና የልኡክ ቡድን አዲስ አበባ መግባቱ አይዘነጋም።

የዛሬው የቻይና መንግስት ድጋፍ የሙቀት መለኪያዎች፣ የእጅ ጓንቶች፣ የጫማ መሸፈኛዎች፣ ማስኮች፣ የህክምና አልባሳት ይገኙበታል።

የሀገራቱ ተወካዮችም ለድጋፉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በምስክር ስናፍቅ

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.