የአዲስ አበባና ሸገር ከተማ አስተዳደሮች በደኅንነት ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ሸገር ከተማ አስተዳደሮች በሠላም እና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የስምምነት ሠነድ ተፈራረሙ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ቡዜና አልቃድር ፣ የሸገር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) ፣ የአዲስ አበባ ከተማ የሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ ፣ በየደረጃው የሚገኙ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የሃይማኖት አባቶች እና አባገዳዎች በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተገኝተዋል፡፡
በመድረክ ሁለቱን ከተሞች በጋራ መሥራት የሚያስችላቸው ሠነድ ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ቡዜና አልቃድር፥ የሕዝብን ሠላምና ደኅንነትን ለማስጠበቅ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ኢኖሚያዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በኃላፊነትና በተጠያቂነት መሥራት ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ የሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ሊዲያ ግርማ በበኩላቸው ÷ “ከአጎራባች የሸገር ከተማ አስተዳደር ጋር በምናከናውነው ጠንካራ ሠላም እና ፀጥታን የማስጠበቅ ሥራዎች ኅብረተሰቡን እያሳተፍን ነው” ብለዋል።
የሸገር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) ÷ ወንጀል ፈፃሚዎችን በጋራ በመከላከል የሕዝቡን አንድነት በማጠናከር የመረጃ ልውውጦችን በቅንጅት በመሥራት ላይ እንገኛለን ማለታቸውን የአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡