Fana: At a Speed of Life!

በአማራና አፋር ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የሚኖሩ ሕዝቦችን ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራና አፋር ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ያለውን የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑ ተጠቆመ።

በአማራና በአፋር ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች የሚኖሩ ሕዝቦችን የእርስ በርስ ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ የውይይት መድረክ ዛሬ በኮምቦልቻ ከተማ ተካሄዷል፡፡

የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ የግጭት ዘላቂ መፍትሔ ትግበራ ባለሙያ አቶ ምስጋናው እንየው÷ የሁለቱን ክልሎች ሕዝቦች ግንኙነት በማጠናከር ሰላማቸውን በጋራ እንዲጠብቁ በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

አዋሳኝ አካባቢዎችም አልፎ አልፎ የሚስተዋሉ ችግሮችን በአገር በቀል እውቀት እንዲፈቱ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ክልሎቹ የሕዝቡን ትስስር በልማት ጭምር ለማቆራኘት በመስራት ላይ ይገኛሉ ያሉት አቶ ምስጋናው÷ የተጀመሩት ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመልክተዋል።

የአፋር ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ተወካይ አቶ ኡመር መሐመድ በበኩላቸው÷ “አዋሳኝ አካባቢ የሚኖሩ ወንድምና እህት ሕዝቦችን በንግድ፣መንገድና ሌሎችም ልማቶች በማስተሳሰር ግንኙነታቸውን ለማጠናከር እየተሰራ ነው” ብለዋል።

አልፎ አልፎ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በባህላዊ እርቅ፣ ጎሳ መሪዎች፣ “አበጋሮች” እና በሃይማኖት አባቶች አማካኝነት እንዲፈቱና መፍትሔ እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

በሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታ ባለሙያ ወ/ሮ ዘይነባ ሱንከሞ÷ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንና አገራዊ አንድነት እንዲጠናከር ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ሕብረተሰቡም ሀገር በቀል እውቀቶችን አዳብሮና ጠብቆ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት የተጀመረው የልማት ጉዞ እንዲቀጥል አመልክተዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች ችግሮችን በባህላዊ ሽምግልናና በውይይት በመፍታት የእርስ በእርስ ግንኙነት በማጠናከር ሰላማችንን ለመጠበቅ ቁርጠኛ ነን ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በውይይቱ ላይ ከአማራና አፋር ክልሎች የተወጣጡ የሃይማኖት አባቶች፣አገር ሽማግሌዎች፣የጎሳ መሪዎችና በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች እንዲሁም የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.