ኪየቭ ከባድ የሚሳኤል እና የድሮን ጥቃት እንደተፈጸመባት አስታወቀች
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የዩክሬን ዋና ከተማ ኪየቭ ከባድ የሚሳኤል እና የድሮን ጥቃት እንደተፈፀመባት የሀገሪቱ ባለስልጣናት ገለጹ።
ድሮኖች እና ሚሳኤሎች ጥቃት ባደረሱበት አካባቢ በትንሹ 3 ሰዎች መቁሰላቸውንም ባለስልጣናቱ ተናግረዋል።
ባለስልጣናቱ የዩክሬን የአየር መከላከያ ወደ ኪየቭ የተወነጨፉ 18 ሚሳኤሎችን መትቶ መጣሉንም ነው የገለጹት።
ዩክሬን በደቡባዊ ግንባር ለሩሲያ አፀፋዊ ምላሽ ከመስጠቷ ቀደም ብሎ ሩሲያ ባለፉት ሳምንታት የአየር ጥቃት ዘመቻዋን ማጠናከሯን መገናኛ ብዙሃን ወታደራዊ ምንጮችን ዋቢ አድርገው እየዘገቡ ነው።
የዩክሬን ጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ቫለሪ ዛሉዢኒ እንደተናገሩት፥ ሩሲያ ከሰሜን፣ ደቡብ እና ምስራቅ አቅጣጫ በኪየቭ ላይ ጥቃት አድርሳለች፡፡
ከአየር፣ ከባህር እና ከየብስ ላይ የተነሱ 18 የሚሳኤል ጥቃቶች መፈፀማቸውን የገለፁ ሲሆን÷ ሁሉም ሚሳኤሎች በዩክሬን ተመተው ወድቀዋል ብለዋል፡፡
የዩክሬን ዋና ከተማ ወታደራዊ አስተዳደር ኃላፊ ሰርሂ ፖፕኮ በበኩላቸው ጥቃቱን “በአጭር ጊዜ ውስጥ የተፈፀመ ከባድ የሚሳኤል ጥቃት ” ሲሉ መግለፃቸውን የቢቢሲ ዘገባ አመላክቷል፡፡
ከንቲባ ቪታሊ ክሊችኮ የሮኬት ስብርባሪ በከተማዋ መካነ አራዊትን ጨምሮ በማዕከላዊ የሀገሪቱ ግዛቶች መውደቁን ጠቅሰዋል።
ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያን ጨምሮ የሶሎሚያንስኪ ግዛት ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበትም ነው የተናገሩት።
የሩሲያ -ዩክሬን ጦርነት ከጀመረ ጀምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ሲቪሎች እና ወታደሮች ህይወታቸውን አጥተዋል አልያም ቆስለዋል፡፡
በከተሞች በርካታ ውድመት ሲከሰት ወደ 8 ነጥብ 2 ሚሊየን የሚጠጉ ዩክሬናውያን በአውሮፓ በስደተኛነት ተመዝግበዋል፤ ከእነዚህ ውስጥ 2 ነጥብ 8 ሚሊየን የሚሆኑት ሩሲያ ውስጥ እንደሚገኙ ተጠቁሟል።