ከ25ኛ ሳምንት በኋላ ያሉ ጨዋታዎች የዲ ኤስ ቲቪ ቀጥታ ስርጭት ሽፋን አያገኙም – ሊግ ኩባንያው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ25ኛ ሳምንት በኋላ ያሉ ጨዋታዎች የዲ ኤስ ቲቪ ቀጥታ ስርጭት ሽፋን እንደማያገኙ የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግ አክሲዮን ማህበር አስታወቀ፡፡
ማህበሩ በማህበራዊ ትስስር ገፁ እንዳስታወቀው ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 2015 ውድድር በሐዋሳ ከተማ እየተካሄደ መሆኑን እና ውድድሩ በቀጥታ የሱፐር ስፖርት ሽፋን እያገኘ እስከ 24ኛ ሳምንት መርሐ ግብር በመካሄድ ላይ ይገኛል።
ይሁን እንጅ አክሲዮን ማህበሩ ከመልቲ ቾይዝ አፍሪካ (ዲ ኤስ ቲ ቪ) ጋር ባለው ውል መሰረት ከ25ኛ ሳምንት በኋላ የሚደረጉ ጨዋታዎች የቀጥታ የቴሊቪዥን ስርጭት ሽፋን እንደማያገኙ አስታውቋል።
ጨዋታዎቹ በቀጥታ ስርጭት ባይተላለፉም በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር በኩል የቪድዮ ቀረፃ ተከናውኖ ለአስፈላጊው አገልግሎት ጥቅም ላይ እንዲውሉ ይደረጋል ብሏል።
በተጨማሪም የሊግ ውድድሩ የመጨረሻ ሳምንታት ጨዋታዎች በቀጥታ ስርጭት በሱፐር ስፖርት እንደሚተላለፉም ነው ያስታወቀው።