አቶ ደመቀ መኮንን ከሳዑዲ አረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከሳዑዲ አረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልዑል ፌይሰል ቢን ፋርሃን አል ሳዑድ ጋር በስልክ ተወያዩ፡፡
አገራቱ ያላቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከርና በሳዑዲ አረቢያ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ በትብብር ለመስራት መስማማታቸውም ተገልጿል።
በውይይቱ ሳዑዲ አረቢያ በሱዳን ወቅታዊ ጉዳይ ከስምምነት ለይ እንዲደርስ እያደረገች ያለውን ጥረት አስመልክቶ አቶ ደመቀና ልዑል ፌይሰል ሀሳብ ተለዋውጠዋል።
አቶ ደመቀ÷የሱዳን ወገኖች፣ ሳዑዲ አረቢያና አሜሪካ የጅዳ ስምምነት እንዲፈረም የተወጡትን ሚና አድንቀዋል።
ኢትዮጵያ ሱዳን ራሷ በባለቤትነት በምትመራው ሂደት ወደ ሰላማዊ መፍትሔ እንድትመጣ ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኗን ለሳዑዲ አረቢያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገልጸውላቸዋል።
ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘም በአፍሪካ ሕብረት የሚመራውን የሶስትዮሽ የግድቡ ድርድር ሊደገፍና ሊከበር እንደሚገባው አቶ ደመቀ አስገንዝበዋል።
የአረብ ሊግ ለኢትዮጵያና ለተቀረው አፍሪካ አህጉር ትልቅ ጠቀሜታ ባለው የሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ላይ የሚያወጣቸው ማንኛውም መግለጫዎች ለሶስትዮሽ ድርድሩ አሉታዊ ተጽእኖ የሚያሳድር መሆን እንደሌለበትም አመልክተዋል።
ሁለቱ ወገኖች የጋራ ፍላጎታቸው በሆኑ የተለያዩ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡