አመራር በመግደል የአማራ ክልልን ችግር መፍታት አይቻልም – ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 10 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) “ፈተናዎችን ወደ እድል በመቀየር ህዝባችንን እናሻግራለን” በሚል መሪ ቃል የአማራ ክልል የከፍተኛና መካከለኛ አመራር ኮንፈረንስ በባህር ዳር ተጀምሯል።
በኮንፈረንሱ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ፥ ክልሉን መሪ በማሳጣትና የክልሉን ህዝብ ሰላም በመናድ የሚመጣ ውጤት አይኖርም ብለዋል፡፡
አመራር በመግደል የአማራ ክልልን ችግር መፍታት አይቻልም ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ለህዝብ የተገቡ ቃሎች ቆጥሮ ለመፈጸም ርብርብ ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
“በጽንፈኞች አጀንዳ እየተመራን ከልማት እና ከብልጽግና ጉዟችን ልንገታ አይገባም” ብለዋል።
“ያጋጠመን ችግር ውስብስብና አስቸጋሪ ነው፤ይህንኑ በጥልቀት በመገምገም እና ለመፍትሔዎቹ አቅጣጫ የሚያስቀምጥ ኮንፈረንስ በማስፈለጉ ምክንያት” መድረኩ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
ብልጽግና ፓርቲ የአማራን ህዝብ ጥያቄዎች ለማስመለስ በሂደት ላይ ያለና ለተፈጻሚነቱ እየተጋ ያለ ፓርቲ መሆኑንም ገልጸዋል።
የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ጋሻው አወቀ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ የአማራ ህዝብ መሰረታዊ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ ትግል ይደረጋል ነው ያሉት።
በክልሉ የገጠመንን ችግር በውል ተረድቶ ወደ ዕድል በመቀየር ከልሉን በብቃት የሚመራ ፓርቲ እና መንግስት በመኖሩ ለዚሁ ዓላማ የሚታገል ቁርጠኛ አመራር እና አባል እንዲሁም ህዝብን የሚያነሳሳ የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ስራ ይሰራልም ብለዋል፡፡
ኮንፈረንሱ የፓርቲውን አመራር እና አባል በክልሉ ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በመድረኩ ከ1ሺህ 400 በላይ በክልሉ የሚገኙ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች ተሳታፊ መሆናቸውን የፓርቲው መረጃ ያመላክታል፡፡
ኮንፈረንሱ በቅርቡ ህይወታቸውን ላጡት ለአቶ ግርማ የሽጥላ እና አብረዋቸው ለተሰው ወንድሞች የጧፍ ማብራት ስነ ስርዓት በማካሄድ መጀመሩ ተጠቁሟል፡፡