Fana: At a Speed of Life!

በእርግዝና ወቅት የሚያጋጥም የደም ግፊት መንስዔ እና ምልክቶች

 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በእርግዝና ወቅት የሚያጋጥም የደም ግፊት እርግዝናን ተከትሎ የሚመጣና ከአራት ወር ተኩል ጀምሮ እስከ 9 ወር እንዲሁም አንድ እናት ከወለደች እስከ ስድስተኛ ሳምንት ይከሰታል።

ጥናት እንደሚያመላክተው በዚህ ሳቢያ በዓለም ላይ በዓመት እስከ 63 ሺህ የሚሆኑ እናቶች እንዲሁም ግማሽ ሚሊየን የሚሆኑ ህፃናት ህይወታቸውን ያጣሉ፡፡

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የማህፀንና ፅንስ ህክምና ክፍል በረዳት ፕሮፌሰርነት የእናቶችና ህፃናት ክትትል ባለሙያ ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት ዶክተር ሰይድ አራጌ እንዳሉት፥ ሶስት አይነት በእርግዝና ወቅት የሚያጋጥም የደም ግፊት ደረጃ አለ።

አንደኛው ከፍተኛ ደረጃ የሚባለው ሲሆን ወዲያውኑ እናት እንድትወልድ ለማድረግ የሚያስገድድ ሲሆን፥ የሚጥል፣ ሳንባን፣ ጉበትንና ኩላሊትን የሚነካ ደረጃ ሲደርስ የልጁን ህይወት የሚያጠፋ ደረጃ ሲደርስ፣ እናት ላይ የደም መቅጠን ካጋጠመ ከፍተኛ ደረጃ እንደሚባል ያስረዳሉ፡፡

ይህም በእርግዝና በየትኛው ወራት ውስጥ እንደሚከሰት ማወቅ እንደማይቻል ዶክተር ሰይድ ይናገራሉ፡፡

በእርግዝና ወቅት የሚያጋጥም የደም ግፊት መንስኤዎች ጥቁር መሆን (black african)፣ ከፍተኛ ክብደት፣ የስኳር በሽታ፣ ከእርግዝና በፊት የደም ግፊት ያለባቸው፣ የኩላሊት በሽታ ያለባቸው፣ እርግዝና እንዲከሰቱ የሚደርጉ ቴክኖሎጂዎች፣ መንታ ልጅ ማርገዝና በቤተሰብ ምክንያት መሆናቸውንም ነው የሚያስረዱት።

በእርግዝና ወቅት የሚያጋጥም የደም ግፊት ምልክቶች ከፍተኛ የሆነ የእራስ ምታት ህመም ፣ የዓይን ብዥታ፣ በእጅ፣ እግርና ፊት ላይ እብጠት፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ የክብደት መጨመር፣ ከአምስት ወራት የእርግዝና ጊዜ በኋላ የሚከሰት ማስመለስ ፣ በቀኝ ጡት ስር ህመም፣ ትንፋሽ ማጠር፣ እራስን ስቶ መውደቅ እና ማንቀጥቀጥ ናቸው፡፡

ይህ ምልክት ሲታይ በፍጥነት ወደ ህክምና ተቋም መሄድ እንደሚያስፈልግ የህክምና ባለሙያው መክረዋል፡፡

እንደ እርሳቸው ገለጻ በእርግዝና ወቅት የሚያጋጥም የደም ግፊት በጊዜ ካልታከመ ልጅ ሆድ ውስጥ እንዳለ ለህልፈት ይዳረጋል፣ ቋሚ ለሆነ የደም ግፊትና ለስኳር በሽታም ይዳርጋል፡፡

ከእርግዝና በፊት ክብደትን መቆጣጠር፣ የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ አመጋገብን ማስተካከል (ጣፋጭ ነገሮችን መቀነስና አትክልትና ፍራፍሬን መመገብ) ፣ ሲጋራ አለማጨስ በእርግዝና ወቅት የሚከሰትን የደም ግፊት ለመከላከል እንደሚያግዙም ዶክተር ሰይድ አራጌ ይናገራሉ፡፡

በእርግዝና ወቅት የሚያጋጥም የደም ግፊት በዓለም ላይ ለእናቶች ሞት ምክንያት ከሆኑ አምስት በሽታዎች መካከል ነው፡፡

በኢትዮጵያም 10 በመቶው ለእናቶች ሞት ምክንያት የሆነው በእርግዝና ወቅት የሚያጋጥም የደም ግፊት መሆኑ ይነገራል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.