የሀገር ውስጥ ዜና

በትግራይ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትን ለማሳለጥ የሲቪል ማኅበራት ሚና የጎላ ነው ተባለ

By Alemayehu Geremew

May 18, 2023

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 10 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ለማድረስ እና የልማት ሥራዎችን ለማሳለጥ የሲቪል ማኅበራት ሚና የጎላ መሆኑ ተገለጸ።

የሲቪል ማኅበራት ባለሥልጣናት እና የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት አመራሮች በትግራይ ክልል የሁለት ቀናት የሥራ ጉብኝት አካሂደዋል፡፡

በቆይታቸውም የሲቪል ማኅበራት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ጂማ ዲልቦ ደንበል እና የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ም/ቤት ዋና ዳይሬክተር ሄኖክ መለሰ ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አባላት ጋር መክረዋል፡፡

የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር በመወከል የተገኙት ጀነራል ጻድቃን ገብረትንሳዔ ÷ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ለሚሠሩት ሥራ ምቹ ምኅዳር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

በዘርፉ ያሉ ድርጅቶች በሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት፣ በሠላም ግንባታ እንዲሁም ልማት ላይ በሚደረጉ ሥራዎች ሳይታክቱ ርብርባቸውን እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

አመራሮቹ በሰባካሪ የተፈናቃዮች ማቆያ እና በትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃዮችን ጎብኝተዋል፡፡

በዚህም አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ እና መልሶ የማቋቋም ሥራ ሊሰራ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

በክልሉ ከሚገኙ የተለያዩ የሲቪል ማኅበራት ተወካዮች ጋር ውይይት ማድረጋቸውም ተጠቁሟል፡፡

በውይይት መድረኩ ÷ በክልሉ የሚገኙ የሲቪል ማኅበራት እና ድርጅቶች በኅግ ማዕቀፍ ውስጥ መሥራት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡

ወደ ሥራ ለመመለስ በሚያደርጉት ጥረትም በሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶች ላይ ውይይት ተደርጎ የመፍትሄ አማራጮች ላይ ሃሳቦችን መለዋወጣቸውን ከም/ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡