የሚኒስትሮች ሶስተኛ ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ተጀመረ
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 10 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሚኒስትሮች ሶስተኛ ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ መጀመሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስታወቁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷”በተቋማዊ አሠራር ላይ ያለውን ሂደት ለመገምገም ባለን ቁርጠኝነት የሚኒስትሮችን የሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ጀምረናል” ብለዋል።
የግምገማ ሂደቱም በአጠቃላይ የ9 ወራት የማክሮ ኢኮኖሚውን እና የሴክተሮች ልዩ አፈጻጸምን ይዳስሳል ነው ያሉት።
በመድረኩ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)÷ የበጀት ዓመቱን 9 ወራት አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል።
በዚህም ባለፉት 9 ወራት በዓለም አቀፍ ገበያ ያሉ አለመረጋጋቶችን በመቋቋም በዋና ዋና የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸም የተሻለ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።
ለአብነትም ባለፉት 9 ወራት ከወጪ ንግድ 2 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር ተገኝቷል ነው ያሉት።
ይህም የዕቅዱን 71 በመቶ መሳካቱን የሚያመላክት ሲሆን÷ በወጪ ንግድ ከተገኘው ገቢ የግብርና ዘርፍ ቀዳሚውን ደረጃ ይይዛል ብለዋል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከቡና ምርት 897 ሚሊየን ዶላር መገኘቱንም በአስረጂነት አቅርበዋል።
መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ሳይጨምር በግለሰቦች በሃዋላ 3 ነጥብ 65 ቢሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ መገኘቱንም አንስተዋል።