Fana: At a Speed of Life!

በሽብር ወንጀል በተጠረጠሩት 5 ግለሰቦች ላይ የ8 ቀናት የምርመራ ማጠናቀቂያ ጊዜ ተፈቀደ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት በወሰደው ሕግ የማስከበር ሥራ በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ውለዋል በተባሉ 5 ግለሰቦች ላይ የምርመራ ማጠናቀቂያ የሥምንት ቀናት ጊዜ ተፈቀደ።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት የፖሊስን የምርመራ ሥራዎችንና የተጠርጣሪዎች የመከራከሪያ ነጥቦችን መርምሮ ነው የሥምንት ቀናት የምርመራ ማጠናቀቂያ ጊዜ የፈቀደው።

የፌደራል ፖሊስ መርማሪ ተጠርጣሪዎቹ ፣ ሕገ-መንግስቱንና ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለማፍረስ በማቀድ ፣ ኢ – መደበኛ አደረጃጀት በመፍጠር ተማሪዎችን በመመልመልና ሥልጠና በመስጠት፣ በአመራሮች ላይ ጥቃት ለመፈፀም እና ግድያን ለማስቀጠል ዓላማ ይዘው ሲቀሳቀሱ መንግስት በወሰደው ሕግ የማስከበር ሥራ በቁጥጥር ሥር ውለዋል በማለት የጥርጣሬ መነሻውን ከዚህ በፊት በችሎት አቅርቦ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ተፈቅዶለት ነበር።

በዚህ በተፈቀደለት 14 ቀን ውስጥ የሠራውን ሥራዎችን በትናንትናው ቀጠሮ አቅርቦ ክርክር ተደርጎበታል።
ተጠርጣሪዎቹ መንበረ አለሙ ተከታይ፣ ሲሳይ መልካሙ አበበ ፣ ገብርዓብ አለሙ ዘሪሁን(ዶ/ር) ፣ ተሥፋዬ መኩሪያው አበባው እና ወንዶሰን ተገኝ ተሥፋዬ ይባላሉ።

መንግስት በወሰደው የሕግ ማስከበር ሥራ አራቱ በአማራ ክልል አንዱ ተጠርጣሪ ደግሞ በአ/አ ከተማ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው መርማሪ ፖሊስ ከዚህ በፊት ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ መግለጹ ይታወሳል።

መርማሪ ፖሊስ በተሰጠው የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ውስጥ ከተለያዩ ባንኮች ማስረጃ እንዲመጣ መጠየቁን፣ የተጠርጣሪዎችን የጣት አሻራ ማስነሳቱን የኃላ ታሪካቸውን የመለየት ስራ መስራቱን፣ በወ/መ/ስ/ህ ቁጥር 27/2 መሰረት የተከሳሽነት ቃላቸውን መቀበሉን፣ የቴክኑክና የፎረንሲክ ማስረጃዎችን እንዲመጡለት የሚመለከተውን ተቋም መጠየቁን፣ የማስመጣት ስራ መስራቱን ፣ እና በተወሰኑ ተጠርጣሪዎች መኖሪያ ቤት ባደረገው ብርበራ ሰነዶችን መሰብሰቡን ለችሎቱ አቅርቧል።

ቀሪ ያላቸውን ስራዎች ማለትም የምስክሮችን ቃል ለመቀበል፣ ከባንኮችና ከተለያዩ ተቋማት ማስረጃዎችን የማምጣት ስራ እንደሚቀረው ፣በአማራ ክልል በተፈጸመ የሁከትና አመፅ ማስነሳት ተግባር ላይ የደረሰውን የሰውና የንብረት የጉዳት መጠን የሚገልጹ የምርመራ ውጤቶችን ለማምጣት ፣ ግብረዓበር ተከታትሎ የመያዝ ስራ እንደሚቀረው ጠቅሶ ተጨማሪ የ14 ቀን ጊዜ እንዲሰጠው መርማሪ ፖሊስ የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱን ጠይቋል።

የተጠርጣሪዎች ጠበቆች በበኩላቸው ፥ ”በፖሊስ ቀሪ ተብለው የቀረቡ ጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ዝርዝር ምክንያቶች ከዚህ በፊት በአጭር ጊዜ መሰራት የሚችሉ በመሆኑ ለተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ሆነው መቅረባቸው ተገቢነት የለውም”ሲሉ ተከራክረዋል።

በፖሊስ ”ምስክር ቃል ለመቀበል ተብሎ የቀረበው በደፈና ነው ”ስንት ምስክር ለመቀበል የሚለው ባልተጠቀሰበት ሁኔታ ላይ ተጨማሪ ጊዜ ሊሰጥ አይገባም ”ሲሉ የመከራከሪያ ነጥብ አንስተው ነበር።

ቀሪ ግብረ አበር ለመያዝ ተብሎ የቀረበውን ጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ምክንያትን በሚመለከት ጠበቆቻቸው ቀሪ የሚያዝ ግብረ አበር የለም በማለት ተከራክረዋል።

ተጠርጣሪዎቹ የቤተሰብ አስተዳዳሪ በመሆናቸው የዋስትና መብታቸው ይፈቀድልን ሲሉ ጠይቀዋል።

ካለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ብርበራ ተደርጓብናል የሚሉ አቤቱታዎችንም አቅርበዋል።

መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ ፥ብርበራን በሚመለከት ከፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ አራዳ ምድብ ፍርድ ቤት ተገቢውን የብርበራ ፍቃድ ወስዶ ብርበራ ማከናወኑን በመጠቆም የብርበራ ፍቃዱን ከምርመራ መዝገቡ ጋር ማያያዙን በመግለጽ ፍርድ ቤቱ መመልከት ይችላል ሲል መልስ ሰጥቷል።

በተሰጠው ጊዜ ውስጥ የሰራው ስራ የለም ተብሎ በጠበቆች በተነሳ ነጥብን በሚመለከት በተሰጠው ጊዜ ውስጥ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸው በርካታ ማስረጃዎችን መሰብሰቡን እና ተገቢ ምርመራ ስራ መስራቱን በመጥቀስ ፍርድ ቤቱ የተሰራውን የምርመራ ስራ ከመዝገቡ እንዲመለከትለት ጠይቋል።

ምስክርን በሚመለከት በደፈናው ብቻ ነው የቀረበው ተብሎ የተነሳው የጠበቆች አስተያየት በሚመለከት የምስክርን ማንነት ዝርዝር በሚስጥር የሚያዝ በመሆኑ መግለጽ አይቻልም በማለት መልስ ሰጥቷል።

መርማሪ ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ በዋስ ቢወጡ ምስክርን ሊያስፈራሩና ማስረጃ ሊያሸሹ ይችላሉ የሚል ስጋት እንዳለው እና በድጋሚ ሁከትና ብጥብጥ በማስነሳት በሰላም ወጥተው በሰላም መግባት የሚፈልጉ ህዝቦች ላይ አደጋ ሊያደርሱ እና ወደ ውጭ ሀገር ሊሸሹ ይችላሉ በማለት ስጋቱን ገልጾ የዋስትና ጥያቄያቸውን በመቃወም ተከራክሯል።

አጠቃላይ የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ የፖሊስን የምርመራ መዝገብ ተመልክቶ ተገቢ ትዛዝ ለመስጠት ለዛሬ በያዘው ቀጠሮ መሰረት ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ከምርመራውና ወንጀሉ ልዩ ባህሪ አንጻር ተጠርጣሪዎቹ ቢወጡ ምርመራ ሊደናቀፍ ይችላል በሚል ዕምነት የዋስትና ጥያቄያቸውን ውድቅ ማድረጉን መዝገቡን የተመለከቱት ዳኛ አብራርተዋል።

መርማሪ ፖሊስ ምርመራውን አጠናቆ እንዲቀርብ ከጠየቀው የ14 ቀን ውስጥ የ8 ቀን ጊዜ ተፈቅዷል።

5ኛ ተጠርጣሪን በሚመለከት ካጋጠመው የጤና ዕክል አኳያ ከአ/አ ፖሊስ ማቆያ ወደ ፌደራል ፖሊስ ማቆያ እንዲዛወር ባቀረበው አቤቱታ መነሻ መሰረት ፍርድ ቤቱ ወደ ፌደራል ፖሊስ የዕስረኛ ማቆያ እንዲዛወር ትዕዛዝ ተሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.