Fana: At a Speed of Life!

በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ችግኝ ከመትከል ባለፈ ለትውልዱ የበለፀገች ኢትዮጵያን ማስረከብ ዋናው ዓላማችን ነው – አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ችግኝ ከመትከል ባለፈ ለመጭው ትውልድ የለማች እና የበለፀገች ኢትዮጵያን ማስረከብ ዋናው ዓላማችን ነው ሲሉ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ገለጹ፡፡

የግብርና ሳይንስ አውደ ርዕይ አካል የሆነው የተፈጥሮ ሀብት ፓናል ውይይት “አረንጓዴ አሻራችን ለዘላቂ ልማታችን” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ነው፡፡

በመድረኩ አቶ አደም ፋራህ እንደገለጹት፥ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ባለፉት ዓመታት ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ቀርፃ እየሰራች ትገኛለች፡፡

በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር መረዳት፣ መዘጋጀት፣ መትከል፣ መንከባከብ እና መጠቀምን መሰረት በማድረግ ለሃገራችን ዘላቂ ዕድገት ሁላችንም መስራት አለብን ብለዋል፡፡

የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ በአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር ባለፉት አራት ዓመታት 25 ቢሊየን ችግኝ መተከሉን ገልጸዋል፡፡

በተካሄደው ጥናትም ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና አካባቢያዊ ለውጥ ማምጣት መቻሉን አንስተዋል።

“ከኢትዮጵያ አልፎ በጎረቤት ሃገራት የተለያዩ ችግኞች እንደተተከሉና በአሁኑ ወቅት ከጎረቤት ሃገራት እንደ ኬንያ ያሉ ሃገራት ልምድ እንድናካፍላቸው ጠይቀዋልም” ነው ያሉት።

ሁለተኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በቅርብ ቀናት ውስጥ የሚጀመር ሲሆን፥ በሚቀጥለው ዓመት ብቻ 7 ቢሊየን ችግኝ ይተከላል ተብሏል።

በምንይችል አዘዘው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.