Fana: At a Speed of Life!

ቦሪስ ጆንሰን የፊታችን ሰኞ ወደ ሥራ ለመመለስ አቅደዋል

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 16፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን የፊታችን ሰኞ ወደ ሥራ ለመመለስ ማቀዳቸው ተሰማ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኮርና ቫይረስ በሃገሪቱ እያስከተለ ያለውን ችግር ለመቆጣጠር በማሰብ ወደ ስራ ለመመለስ ማሰባቸውን ቴሌግራፍን ዋቢ ያደረገው የሲ ጂ ቲ ኤን ዘገባ ያመላክታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ከሶስት ሳምንት በፊት ሆስፒታል መግባታቸው ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ የሰውነት ሙቀትን ጨምሮ የቫይረሱን ምልክት ማሳየታቸውን ተከትሎ ለንደን በሚገኝ ሆስፒታል ከገቡ በኋላም በጽኑ ህሙማን መከታተያ ገብተው የህክምና ክትትል ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ከቀናት በኋላ የጤና ሁኔታቸው እየተሻሻለ መምጣቱን ተከትሎም ከሆስፒታል እንዲወጡ መደረጉም ነው የተነገረው።

የጤና ባለሙያዎችን ምክር ተከትሎም ቦሪስ ጆንሰን በአፋጣኝ ወደ ስራቸው እንደማይመለሱ ሲነገር ቆይቷል።

አሁን ላይ በሃገሪቱ 139 ሺህ 246 ሰዎች ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን፥ 18 ሺህ 738 ሰዎችም ለህልፈት ተዳርገዋል።

ጆንሰን ለቫይረሱ ወረርሽኝ አዝጋሚ ምላሽ ሰጥተዋል በሚል ከተቀናቃኝ ፖለቲከኞች እና ከአንዳንድ የጤና ባለሙያዎች ትችት አስተናግደዋል።

 

ምንጭ፡-ሲ ጂ ቲ ኤን

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.