የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የአምቡላንስ እና ሰርቪስ ተሸከርካሪዎች ተበረከተለት
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 11 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ቀይመስቀል ማህበር አገልግሎቱን ለማስፋፋት የሚረዳ 14 አምቡላንስ እና 9 ሰርቪስ ተሽከርካሪዎች ከዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ማህበር ተበርክቶለታል።
አምቡላንሶቹ 28 ሚሊየን ብር ወጪ እንደተደረገባቸውና ለሰርቪሶቹ ደግሞ 18 ሚሊየን ብር ወጪ መደረጉም ተመላክቷል፡፡
በተጨማሪም በ8 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር ወጪ የተገዙ ደረጃቸውን የጠበቁ የቅድመ ሆስፒታል ህክምና መስጫ ቁሳቁሶችም ድጋፍ መደረጉ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ዋና ፀሐፊ ጌታቸው ታዓ ድጋፉ የአምቡላንስ ቁጥርን ከማሳደግ ባለፈ የአገልግሎት ጥራቱንም ያሻሽላል ብለዋል፡፡
አምቡላንሶቹ በዓመት ግማሽ ሚሊየን ለሚደርስ የህብረተሰብ ክፍል የሚሰጠውን የሰብዓዊ ድጋፍ በእጅጉ እንደሚያግዙም ዋና ፀሐፊው ተናግረዋል፡፡
የተደረገው ድጋፍም የማህበሩን የአምቡላንሶች ቁጥር ወደ አራት መቶ አርባ አራት ከፍ ያደርገዋል ነው ያሉት።
አክለውም 88 ዓመት ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የሁሉንም ድጋፍ እንደሚፈልግም ጠቁመዋል፡፡
በፈቲያ አብደላ