አምባሳደር ሽፈራው ገነቲ ከባህሬን የአሰሪና ሰራተኞች ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ዋና ስራ አስፈጻሚ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 12 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በባህሬን የኢትዮጵያ ቆንስል ጀነራል አምባሳደር ሽፈራው ገነቲ ከባህሬን የአሰሪና ሰራተኞች ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ዋና ስራ አስፈጻሚ ኖፍ አብዱልራህማን ጃምሺር ጋር ተወያይተዋል።
ሁለቱ ወገኖች በባህሬን በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጥበቃ ላይ ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
አምባሳደር ሽፈራው የባህሬን የአሰሪና ሰራተኞች ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ለኢትዮጵያውያን ዜጎች እየሰጣቸው ለሚገኙ አገልግሎቶችና ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን መዋጋትና የኢትዮጵያ ሰራተኞች በወቅቱ ክፍያቸውን የሚያገኙበትን ሁኔታ ማረጋገጥ ላይ በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል።
የባህሬን የአሰሪና ሰራተኞች ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ዋና ስራ አስፈጻሚ ኖፍ አብዱልራህማን ጃምሺር በበኩላቸው፥ ለጉልበት ብዝበዛና ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር የተዳረጉ ሰራተኞች በመጠለያ በማቆየት የሚያስፈልጋቸው ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ገልጸዋል።