Fana: At a Speed of Life!

ጀጁ ኮፊ በኢትዮጵያ ቡና ላይ ጥናቶችን ለማድረግ እና እሴት የመጨመር ፍላጎት እንዳለው ገለፀ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 12 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ኮሪያው ቡና አምራች ኩባንያ ጀጁ ኮፊ በኢትዮጵያ ቡና ላይ ጥናቶችን ለማድረግ እና እሴት የመጨመር ፍላጎት እንዳለው ገለፀ፡፡

በደቡብ ኮሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሴ ዳልኬ በደቡብ ኮሪያ ከሚገኘው ጀጁ ቡና አምራች ኩባንያ ዋና ስራ አስፈፃሚ ከሆኑት ኪም ያንግ ሀን ጋር ተወያይተዋል፡፡

አምባሳደር ደሴ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ኢትዮጵያ የቡና መገኛ ሀገር መሆኗን እና የኢትዮጵያ ቡና ከሌሎቹ ሀገራት ቡናዎች በተለየ የቸኮሌት ጣዕም ፣ የፍራፍሬ ጣዕም እና ጥሩ መዓዛ ያለው ቡና መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቡና እሴት ከተጨመረበት በዓለም ላይ የሚኖረው ተቀባይነት ከፍተኛ መሆኑን ነው  አምባሳደሩ የገለፁት፡፡

ኪም ያንግ በበኩላቸው÷የኢትዮጵያ ቡና ከሌሎች ሀገራት ቡናዎች የተሻለ ጣዕም ያለው ቡና መሆኑን እገነዘባለሁ ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ቡና ላይ ጥናት ማድረግ እንደሚፈልጉ የገለፁት  ኪም ከኢትዮጵያ ቡና የወይን መጠጥ እና የመዋቢያ ቁሳቁሶችን ማምረት እንደሚፈልጉ ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቡናን ተወዳጅነት ለማሳደግ በደቡብ ኮሪያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ  ትብብር እንዲያደርግ መጠየቃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.