Fana: At a Speed of Life!

ወባን ለመቆጣጠርና ለማጥፋት በጤና ሚኒስቴርና በአጋር አካላት መካከል ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 16፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ወባን ለመቆጣጠርና ለማጥፋት በጤና ሚኒስቴርና በአጋር አካላት መካከል ስምምነት ተፈረመ።

ስምምነቱን የጤና ሚኒስትር ዲኤታው ዶክተር ደረጀ ዱጉማ ፈርመውታል።

ሚኒስትር ዲኤታው ወባን የማስወገዱ ተግባር በመላ ሀገሪቱ እየተከናወነ መሆኑን አስታውሰው ከኮሮና ቫይረስ መከሰት ጋር ተያይዞ የወባ ወረርሽኝ የበለጠ ጉዳት እንዳያደርስ ያለፈውን ስራ ገምግሞ ወደ ቀጣይ ስራ መገባቱ መልካም ነው ብለዋል።

የኮቪድ-19 ቫይረስን እየተዋጋን ወባም ሆነ ሌሎች በሽታዎች ጥፋት እንዳያስከትሉ የሚቻለውን ሁሉ ለማድረግ የአጋር አካላት ድጋፍ ትርጉም እንዳላቸውም ጠቅሰዋል።

ስምምነቱ ባለፉት ሦስት ዓመታት የተከናወኑ ተግባራትና ውጤቶቻቸውን በመገምገም ቀጣዩን ስትራቴጂክ ዕቅድ ለማዘጋጀት የሚደግፍ ነው ተብሏል።

እንዲሁም ከ2021 እስከ 2025 የሚተገበር አዲስ የስትራቴጂክ ዕቅድ እንደሚዘጋጅ መገለፁን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.