አቶ ደመቀ መኮንን ከካናዳ ዓለም አቀፍ የልማት ሚኒስትር ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከካናዳ ዓለም አቀፍ የልማት ሚኒስትር ሃርጂት ሲንግ ሳጃን ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም ÷ በኢትዮጵያ እና ካናዳ መካከል ያለውን ጠንካራ እና የቆየ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል፡፡
አቶ ደመቀ ÷የኢንቨስትመንትና ንግድ ፖሊሲዎችን በማጎልበት እንዲሁም ለቀጠናዊ ኢኮኖሚ ውህደት የሚያግዙ ስትራቴጂካዊ አጋርነቶችን በመፍጠር በሀገር ውስጥም ሆነ በአፍሪካ ቀንድ ልማትን ለማምጣት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
የሀገር ውስጥ የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ እና ዲጂታል 2025 የኢትዮጵያ፣ የለውጥ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ምሰሶዎች፣የወጣቶችን የስራ እድል ፈጠራና የሴቶችን ተጠቃሚነት በማጎልበት ላይ መሆናቸውንም ገልፀዋል።
በዚህ ረገድ እንደ ካናዳ ያሉ ዓለም አቀፍ አጋሮች ሰላም የየትኛውም የልማት እንቅስቃሴ የጀርባ አጥንት በመሆኑ የኢትዮጵያን የልማት ጥረትና የተጀመረውን የሰላም ሒደት እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ሁለተኛውን ሀገር -በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ተግባራዊ ለማድረግ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑም አስረድተዋል፡፡፡
በተለይም በግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝም እና ታዳሽ ኃይል የመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ለዓለም አቀፍ ባለሃብቶች እና የልማት አጋሮች ምቹ ሁኔታን በመፍጠር በተጠቀሱት ቁልፍ ቦታዎች ያልተነካውን እምቅ አቅም ለመጠቀም ያስችላል ብለዋል።
ሃርጂት ሲንግ ሳጃን በበኩላቸው÷ የኢትዮ-ካናዳ የልማት ትብብር ለረጅም ዓመታት የዘለቀ መሆኑን አውስተው፣ ይህንኑ ለማስቀጠል እንደሚሠሩ ቃል ገብተዋል።
የምግብ ዋስትናን ማሻሻል እና የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የታቀዱ ውጥኖችን ለመደገፍ የካናዳ መንግስት ያለውን ፍላጎት መግለፃቸውንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።