የተፈጥሮ አደጋዎችን ለመከላከል የተጠናከረ የቅድመ ማስጠንቃቂያ ስርዓት መዘርጋት እንደሚገባ ተመለከተ
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 15 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአየር ንብረት ለውጥ አማካኝነት የሚከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎችን ለመከላከል የተጠናከረ የቅድመ ማስጠንቃቂያ ስርዓት መዘርጋት እንደሚገባ ተገለጸ፡፡
19ኛው የዓለም ሜቲዮሮሎጂ ድርጅት ኮንግረስ በጀኔቫ ስዊዘርላንድ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
በኮንግረሱ እየተሳተፉ የሚገኙት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አብርሃ አዱኛ (ዶ/ር) እንደገለጹት÷ የአየር ንብረት ለውጥ ድርቅ፣ የጎርፍ አደጋ፣ የደን ቃጠሎና የመሬት መንሸራተት የመሳሰሉ ተፈጥሯዊ አደጋዎች መንስዔ በመሆን የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ ከባድ ጫና ፈጥሯል፡፡
ለዚሀም በኢትዮጵያ በደቡብና በደቡብ ምስራቃዊ አካባቢዎችና በአጎራባች ሀገራት ለተከታታይ አምስት አመታት የተከሰተው ድርቅ በሰዎች ላይና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ጠቅሰዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው እንደሚሉት ÷በአየር ንብረት መዛባትና ለውጥ ምክንያት የሚመጡ ችግሮችን ለመቋቋም መወሰድ ከሚገባቸው እርምጃዎች መካከል አንዱ የተጠናከረ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓት በመዘርጋት መረጃ ቀድሞ እንዲደርስ ማድረግ ነው፡፡
የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓቱ የተጠናከረ የሃይድሮ-ሜቲዮሮሎጂ መከታተያና መቆጣጠሪያ መሠረተልማት እንዲሁም የዘርፉ ተዋናዮችን ቅንጅት እንደሚፈልግም ነው ያነሱት፡፡
በፈረንጆች አቆጣጠር ከግንቦት 22 እስከ ሰኔ 2 ቀን 2023 በሚቆየው በዚህ ኮንግረስ ሚኒስትር ዴኤታውን ጨምሮ፥ የኢትዮጵያ ሜቲዮሮሎጂ ኢኒስቲቲዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ እና ሌሎች የስራ ሃላፊዎች ተሳታፊ መሆናቸውን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡