Fana: At a Speed of Life!

የምንከተለው አቅጣጫ የቤንሻንጉል ጉሙዝን ህዝብን የክህሎት ልማትን መሠረት ያደረገ የሥራ ዕድል ፈጠራ ነው – ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የምንከተለው አቅጣጫ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህዝብ ምርታማነትን ለመጨመር የሚያስችል የክህሎት ልማትን መሠረት ያደረገ የሥራ ዕድል ፈጠራ ነው ሲሉ የሥራና ክኅሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ተናገሩ፡፡

የቀጣይ ወራት የክኅሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራ ልዩ የንቅናቄ ዕቅድ ላይ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይት ተካሂዷል፡፡

በአሶሳ በተካሄደው ውይይት የኢፌዴሪ የሥራና ክኅሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚልን ጨምሮ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን እና የክልሉ አመራሮች ተገኝተዋል።

የሥራና ክኅሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ÷ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በክኅሎት ልማቱና በሥራ ዕድል ፈጠራው መሥክ አበረታች ውጤት የተገኘ ቢሆንም አመርቂ አይደለም ብለዋል።

ክልሉ የታደለውን የተፈጥሮ ሐብት አልምቶ ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግና ላይ ገና ብዙ መሥራት እንደሚቀርም ነው ያመላከቱት፡፡

በመሆኑም የክልሉ አመራሮች “ክኅሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራ ዕቅዱ”ን ለማሳካት ተሰናስለው መረባረብ እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡

ምርታማነት ለመጨመር የክኅሎት ልማትን መሠረት ያደረገ የሥራ ዕድል ፈጠራን ማዕከል ማድረግ እንዳለባቸው መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ርዕሠ-መስተዳድር አቶ አሻድሉሌ ሐሰን በበኩላቸው ÷ የክኅሎት ልማት እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ጉዳይ የአንድ ሴክተር መሥሪያ ቤት ተግባር አይደለም ብለዋል፡፡

እንደ ክልል ከድህነት ለመውጣትና ልማትን በቀጣይነት ለማረጋገጥ ዘርፉ በምክትል ርዕሰ – መስተዳድሩ እንዲመራና አደረጃጀቱም እንዲስተካከል የማድረግ ሥራዎች እየተሰሩ ነውም ብለዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.